ኢትዮጵያ የፌደራል ሥርዓትን የምትከተል አገር አይደለችም – ገለታው ዘለቀ


ትግራይ-ልዩ-ሃይል2-150x150ኢትዮጵያ ሆይ የአስተዳደር ዘየሽ ምን ይመስላል? ተብላ ብትጠየቅ በዓለም ላይ የፌደራል ስርአትን ከሚከተሉ አገራት አንዷ ነኝ ስሜም የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግስት ይባላል ትላለች። በርግጥ በዓለም ላይ ካሉ ብዙዎቹ ሃገራት የፌደራል ስርአትን አይከተሉም። ብሪታኒያን ፈረንሳይን ጨምሮ በዴሞክራሲ የበለጸጉ አንዳንድ አገራት የአሃዳዊ አስተዳደር ዘየን ይከተላሉ። በአንፃሩ የፌደራል ስርአትን የፈጠረችውን የተባበረችውን አሜሪካንን ጨምሮ አውስትሬሊያ ካናዳና ብራዚልን የመሳሰሉ አገሮች የፌደራል ስርአትን ይከተላሉ። እንግዲህ ታዲያ አሃዳዊ ስርአትን የሚከተሉም ይሁኑ ወይም የፌደራል ስርአት የሚከተሉ እንዳንዶች ዴሞክራት አንዳንዶች ደግሞ ገና ዴሞክራሲ ያላደገባቸው ሆነው ይታያሉ። ብቻውን አሃዳዊ ወይም ፌደራላዊ መሆን ለዴሞክራሲም ለመልካም አስተዳደርም ዋስትና አይሆንም። መሪዎች የፓለቲካ ቁርጠኝነት ከሌላቸውና የዴሞክራሲ ባህል ካልዳበረ ጥሩ የአስተዳደር ስርአት ብቻውን ፋይዳ የለውም። በርግጥ ለዴሞክራሲ ስርዓት የቆረጡ ፓለቲከኞች ደግሞ ለዴሞክራሲ ስርዓት ማንሸራሸሪያ የሚሆን የተሻለ ሲስተም መፍጠር አለባቸው። ስርአት ብቻውን ምንም አይሰራም እንበል እንጂ ከዴሞ ክራሲ ጋር ሆኖ አንድ ስርአት ከሌላው የተሻለ ውጤት ሊያመጣ ይችላልና ከስርአት ስርአት መምረጥ ተገቢ ነው። ለምሳሌ በአሁነ ሰአት ያለው የኢትዮጵያ ችግር የመንግስት ለዴሞክራሲ መዳበር አለመቁረጥ ብቻ ሳይሆን የሲስተም ችግርም አለው። ሲስተሙ ዴሞክራሲን እንዴት እየጠለፈ እንደሚጥለው ወደ ኋላ ላይ በስፋት እናያለን።

ወደ ኢትዮጵያ የመንግስት አወቃቀር እንመለስና በርግጥ ኢትዮጵያ በአሁኑ ሰአት ፌደራል ነኝ እንደምትለው በርግጥ የፌደራል ስርአትን እየተከተለች እንደሆነ ልንፈትሻት ይገባል። በመሰረቱ አንድ አገር የፌደራል ስርአትን መርጫለሁ ሲል የፌደራል ስርአትን የፍልስፍና መሰረቶች አምኜባቸዋለሁ ተግባራዊ እያደረኳቸው ነው ማለቱ ነው። ኢትዮጵያ በርግጥ የፌደራል ስርአትን መከተል አለመከተሏን ማሳያ ከሚሆኑት የፌደራሊዝም ባህርያት ጋር እያገናዘብን መገምገም አለብን። ለመሆኑ የፌደራል ስርአት መገለጫዎች ምን ምን ናቸው?

የሃይል ክፍፍል

ከብዙ አመታት በፊት አሜሪካውያን አንድ የእስተዳደር ዘየ በራላቸው። የዚህ ዘየ ፍልስፍና መነሻ ሃይልን በፓለቲካ ዩኒቶች መሃል በመከፋፈል መንግስትን ራሱን በመዘርዘር ሰፊ ለሆነችው አሜሪካ መልካም አስተዳደርንና ዴሞክራሲን የበለጠ እናራምዳለን የሚል ነበር። ከመነሻው አሳቡ የመነጨበት ስነ ልቡና ዴሞክራት እንደሆነ መረዳት ይቻላል። ስልጣንን ማጋራትና ወደ ህዝብ ቀረብ ማድረግ ለአምባገነን መሪዎች አስፈሪ ቢሆንም እነዚያ የአሜሪካ ቆራጥ የዴሞክራሲ አርበኞች ግን ስልጣንን በማካፈል የተለየ አስተዳደር ለማምጣት ቀዳሚ ሆኑ።

የፌደራሊዝም አሳብ የያዘው ተልእኮ በአንድ የፓለቲካ መዋቅር ውስጥ በዋናነት ሁለት መንግስታት ተመስርቶ የፌደራልና የስቴት መንግስታት ተፈጥረው እነዚህ ሃይላት የራሳቸው ህገ መንግስት ኖሯቸው ነገር ግን ከዋናው የሃገሪቱ ህገ መንግስት ጋር የማይጣረስ ሆኖ መኖር ለዜጎችም ምርጫን ይጨምራል መልካም ፍክክርን ያመጣል ቅልጥፍና ያመጣል ከሚል ነው። ክልሎች የመለስተኛ አገር ያህል ስልጣን ይዘው የሚሰሩበት ሁኔታ ተፈጠረ ማለት ነው። በአሜሪካ ሁኔታ ሃምሳ መንግስታት ተፈጠሩ ማለት ነው። መንግስት የሚለው ጽንሰ ሃሳብ ተዘረዘረ ማለት ነው። በተለምዶ አንድ ጠቅል መንግስት የነበረውን ወደ ሃምሳ መንግስታትን የያዘ አንድ የፌደራል መንግስት ተፈጠረ ማለት ነው። መንግስት ሃይሉን ዘርዝሮ ሲሰራበት የበለጠ ያተርፋል። የበለጠ ይወልድለታል። የህግ ሪሶርሶች ይጨምራሉ። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶች ይበዛሉ። ተመሳሳይ ችግሮች በተለያየ ክልል ምክር ቤት ሲታዩ የተሻለ ምርጥ አሳብ ለማግኘት ይረዳል። በብዙ ጠረንጴዛ ዙሪያ የሚደረግ ውይይት የክልልንም የሃገርንም ችግር ለመፍታት ትልቅ ሃይል ነው። የህዝብን ተሳትፎ ከፍ ያደርጋል።ለፌደራል መንግስት የማሰቢያ ጊዜ ይሰጠዋል።

አንዱ ሌላው የዚህ የፌደራል ስርአት ፍልስፍና መነሻ ስልጣን አካፈልን ማለት ሃላፊነትን ማካፈል ማለት ነው። ሃላፊነትና ስልጣን አብረው የሚሄዱ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው። ሃላፊነትን አንድ ቦታ ከመከመር ይልቅ ማከፋፈሉ ፈጠራን መነቃቃትን የያገባኛል ስሜት (sense of belongingness) ሁሉ ይጨምራል። የልማት የመልካም አስተዳደር ሃገር የመምራት የሰላም ጉዳዮች ሃላፊነትን ዘርዘር ስናደርግ የበለጠ ምርታማ ይሆናሉ ከሚል ይመስላል። በዘመኑ አገላለጽ የብዝሃነት አስተሳሰብ ውጤትም ነው።

በዚህ መሰረት አንድ ሃገር የፌደራል ስርአት ተከታይ ነኝ ካለ የሚጠየቀው ዋና ጥያቄ ሃይል አካፍለሃል ወይ? ሃላፊነትን አካፍለሃል ወይ? የሚል ነው የመጀመሪያው ጥያቄ። እውነተኛ የሃይል ክፍፍል ከሌለ እውነተኛ ፌደራሊዝም የለም። እውነተኛ የፌደራል ስርአት ከሌለ ደግሞ አለ እያሉ ማውራት ከቶ ለምን ይጠቅማል?

ይህን የሃይል ክፍፍል እንደ ዋና የፌደራል ስርአት መገለጫ አድርገን የኢትዮጵያን የሃይል ክፍፍል መገምገም አለብን። ይህ ግምገማም በርግጥ ኢትዮጵያ የፌደራል ስርአትን እየተከተለች ነው ወይ? የሚለውን ፍንትው አርጎ ያሳየናል።

በፌደራል ስርአት ምስረታ ጊዜ ክልሎች የራሳቸው ህገ መንግስት ይኖራቸዋል። ይህ ህገ-መንግስት ስልጣናቸውን ተግባራዊ የሚያደርጉበት መሳሪያ ነው። በርግጥ ኢትዮጵያ እነዚህ የክልል ህገ መንግስታት ያሏት ሲሆን የፓለቲካው እውነተኛ ሃይል ግን በከፍተኛ ሁኔታ በፌደራል አካባቢ ተከምሮ ይታያል። ይህ የስልጣን ክምር በአብዛኛው ባልተፃፈ ህግ የተዘረፈ ነው።

እንደሚታወቀው የፌደራሉን መንግስት እመራለሁ የሚለው ኢህአዴግ በሃይል በህወሃት ተጽእኖ ስር ወድቋል። ይህ ማለት የፌደራል መንግስቱ ሃይል በህወሃት አካባቢ ነው ማለት ነው። ከፍተኛ የጦሩ መሪዎች የሰኪዩሪቲ መሪዎች የዚህ ቡድን አባላት ሲሆኑ የፌደራሉን ተቋማት መሳሪያ እያደረጉ የሆነ ክብ ሰርተው የዚያን ክብ ኢኮኖሚያዊ አቅም ሲያጎለብቱ ይታያል። የክልል መንግስታት ሃይላቸውን ተገፈው በጣም የደከሙ ስለሆነ ህዝብ በተፈጠሩት ክልሎች ላይ እምነት አጣ። እውነተኛ የሃይል ክፍፍል ኖሮ ቢሆን እውነተኛ የፌደራል ስርአት ስለሚኖር የኦሮሞ ህዝብ በዚህ ደረጃ ባላመፀ። የአማራና የኦጋዴን የሌሎችም ክልሎች ህዝቦች ባላማፁ። ህዝቡ ቀድሞ ነገር የክልል መንግስታትን እንደ ህወሃት መጠቀሚያ ያያል። የህዝቡ እምነት (perception) የሚያሳየው እውነት ደግሞ ሃይል ሲበዛ በህወሃት እጅ ውስጥ መሆኑን ነው። የሚገርመው ነገር ከትግራይ ክልል ውጭ የየትኛውም ብሄር አብዛኛው አባል በተለይ ለሂቁ የቡድናቸው የፓለቲካ ባለስልጣን የህወሃት ቅጥረኛ ነው ብለው ያምናሉ። ኦሮሞዎች፣አማሮች፣ደቡብ ወዘተ ተመሳሳይ እምነት አላቸው። ትግራይ ላይ የሚለየው ነገር የትግራይ ህዝብ ህወሃትን የጠላው ይህ ድርጅት በሌሎች የፓለቲካ ቡድኖች ተጽእኖ አለበት ብለው ሳይሆን የሚያዝኑት ድርጅቱ ዴሞክራሲያዊ ባለመሆኑና ከባህላዊ እሴቶቻቸው የወጣ እሴቶቻቸውን ያላገናዘ በመሆኑ ከሌሎች ቡድኖች ጋር እያጋጨ እየጠቀምኩህ ነው ማለቱ ነው። ይሉኝታውን ሸጦ ማሸማቀቁ አገሩን ሲጎዳ ማየቱ ከወንድሞቹ ሁሉ ለማለያየት መጣሩ ትግራይን ጎድቶታል። ህወሃት ከአማራና ከኦሮሞ ከሌላውም ፈንታ ላይ እየዘረፈ እያመጣ ይሄውልህ ፋብሪካ ሰራሁልህ ይሄው መንገድ ሰራሁ አሁን ከሌሎች ክልሎች እኛ አንደኛ ወጣን………. የተሻለ ለምተናል ሲለው የትግራይ ህዝብ የበለጠ ይጎዳል ያፍራል ይመስለኛል። ይሉኝታ አብሮ መብላት ባህሉ የሆነው ትግራይ ይህ ቡድን ማፈሪያ ሆኖበታል።

ለማናቸውም ግን ይህ የትግራይን ህዝብ እወክላለሁ የሚለው ህወሃት የሃገሪቱን ስልጣን ስለጠቀለለ በተግባር የፌደራል ስርአት አለ ማለት አይቻልም ማለት ነው። ከፍ ሲል እንዳልነው እውነተኛ የሃይል ክፍፍል ከሌለ የፌደራል ስርአት የለምና። ኢትዮጵያ ይህን ሁሉ ሃይል ጠቅልላ ለአንድ ጎጠኛ ቡድን አስረክባ የፌደራል አገር ነኝ ብትል የሚሰማት የለም። ዋናው የፌደራል ስርአት የፍልስፍና መሰረትም የተፈጠረበት አላማም ይሄው ሃላፊነትንና ስልጣንን ማካፈል በመሆኑ ይህንን የከላ አገር ፌደራላዊ መንግስት ነኝ ለማለት ከቶውንም አይችልም።

ማንነት

አንዱ የፌደራል ስርአት ጥቅም እንደ ኢትዮጵያ ብዙ ዘውጎች ባሉበት አገር ዘውጋዊ ማንነትንና ብሄራዊ ማንነትን አጣጥሞ ለማራመድ ስለሚመረጥ ነው። ዘውጋዊ ማንነትና ብሄራዊ ማንነትን እንደ ተቃራኒ ማየት ለሃገር ኣደገኛ ነው። በኢትዩጵያ ሁኔታ ዘውጋዊ ማንነትንና ብሄራዊ ማንነትን በሚገባ ያልተረዱና ያላጠኑ የፖለቲካ ድርጅቶች ሃገሪቱን ወዳልሆነ አቅጣጫ ሊወስዷት ይችላሉ። በመሆኑም በሃገራችን ፖለቲከኞች ህይወት ውስጥ ኣንድ በጥልቀት ሊጠናና የፖለቲካ የፍልስፍና መሰረት ሊሆን የሚገባው ጉዳይ ይህ የብሄር ማንነትና የብሄራዊ ማንነት ጉዳይ ነው። ወደ ኋላ ታሪካችንን ስናይ አገራችን ኢትዮጵያን እነዚህን ሁለት ማንነቶች በሚገባ ያስተናገደችበት ጊዜ የለም። ሁል ጊዜም እንደ ኣጥፊና ጠፊ በማየት ኣንዱ ኣንዱን እየረመረመ እንዲሄድ የሚደረግበት ሁኔታ ነው ያለው። የኢትዮጵያን ታሪክ ስናይ ብሄራዊነት የሚያብበው የብሄሮችን ማንነት በመደፍጠጥ መስሎ ስለታያቸው ለረጅም ጊዜ የብሄሮች ማንነት ተጎድቶ ብሄራዊ ማንነትን ለማፈርጠም ተሞክሯል። ይሁን እንጂ መዋጥ የሚሰማቸው ብሄሮች ማንነታችን ኣደጋ ላይ ነው በሚል ሲታገሉ ኖረዋል። ኢሃዴግ በ 1983 ዓ.ም ስልጣን ከያዘ በሁዋላ ደግሞ ብሄራዊ ማንነትን ጽንፍ ሄዶ በማራከስ ኣካባቢያዊ ማንነት እንዲያብብ ጥረት አድርጓል። በውጤቱም ዛሬ ብሄራዊ ማንነት በአካባቢያዊ ማንነት እየተረመረመ ይገኛል። ዘውጎች ሁሉ የፖለቲካ ጥብቋቸውን ለብሰው ለብሄራዊ ማንነት ጡንቻቸውን በማሳየት ኣንተ ምንድነህ? (ለመሆኑ ኢትዮጵያ ምንድናት እሷ?……..) እስኪሉ የድፍረት ቃል እስኪወጣቸው ብሄራዊ ማንነት ኮስሷል። ይህ ኣንዱ ባንዱ ላይ ጎልብቶ ለመታየት የሚደረግ ጥረት ሃገራችንን እንዳትራመድ ያደረገ፣ የዴሞክራሲ እድገታችን ጠላት ነው። ፖለቲከኞች ልንረዳው የሚገባው እነዚህ ሁለት ማንነቶች የማይገሰሱ የኢትዮጵያውያን መገለጫዎች ናቸው። ሁለቱም እርስ በርስ መረማመድ የለባቸውም። ማሸቀዳደምም ኣይገባም። አንድን ግለሰብ ከክርስትናህና ከኢትዮጵያዊነትህ የቱ ይበልጣል? የቱ ይከተላል? ብሎ መፈተን ተገቢ አይደለም። አንድ ዜጋ እነዚህን ሁለቱንም ማንነቶቹን ኣንደኛ ደረጃ ሰጥቶ እየወደዳቸው ሊኖር ይችላል። ቀድሞውንም ውድድር ውስጥ መግባት የለባቸውም። ልክ እንደዚህ ኣንድ ኦሮሞ ከኦሮሞነትህና ከኢትዮጵያዊነህ የቱ ነው መጀመሪያ? ሊባል ኣይገባም። ሁሉቱም ኣንደኛ ሁነውለት ሳይነቃቀፉ መኖር ይችላሉ። ዋናው ችግር የሚፈጠረው እነዚህ ማንነቶች ሁሉ ኣንድ የፖለቲካ ዮኒፎርም መልበስ ኣለብን ብለው ብቅ ሲሉ ነው። በሃይማኖት ላይ በፖለቲካ መደራጀት ሲጀመር ሃይማኖትና ብሄራዊ ማንነት በአንድ የፓለቲካ የመሮጫ መም ላይ ስለሚገናኙ እነዚህን ሁለት ማንነቶች እንደ ተፎካካሪ እንደ ባላንጣ እንድናያቸው ያደርጋል። ድጋፋችን ወደ አንዱ እንዲያዘም ያደርጋል። ኣገር ማለትም ብሄራዊ ማንነት በተፈጥሮው የሚቆምበት ዋና መሰረት ፖለቲካ በመሆኑ ብሄርና ሃይማኖት ፓለቲካ መሆን ሲያምራቸው ሁለቱም ማንነቶች ማለትም ብሄራዊ ማንነትና ቡድናዊ ማንነት በኣንድ የሩጫ መስመር ላይ ይገናኛሉ። በዚህ ጊዜ ነው ፍክክር የሚገቡት። ፍክክሩ ደግሞ መርህን እየጣሰ ስሜትን እያራገበ ስለሚሄድ የሃገራችንን ህልውና አደጋ ላይ ሊጥልብን ይችላል። በመሆኑም እነዚህን ሁለት ማንነቶች ሳናሽቀዳድም ለመንከባከብ የሚያስችል ራሱን የቻለ ሲስተም ልንቀርጽ ይገባናል። ይህ ሲስተም ሁለቱ ማንነቶች ለየብቻ እንደ ተፈጥሮኣቸው የሚሮጡበትን ስርዓት የሚፈጥር፣ ሁለቱም ማንነቶች ለየብቻ የሚሮጡበትን የሩጫ መም የሚዘረጋ ነው። ያንን ስናደርግ ኣካባቢያዊ ማንነትና ብሄራዊ ማንነት እንደ ባላንጣ ሳይሆኑ እንደ ዋልታና ማገር ሆነው ኣገራችን የረጋችና የጸናች ትሆናለች።

እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ብዙ ብሄሮች ላሏቸው አገራት የፌደራል ስርአት ግጭትን ለመቀነስና ማንነትን ለመጠበቅ ይረዳል ሲባል ብሄራዊ አንድነትንም ባህላዊ ማንነትንም መጠበቅን ያገናዘበ መሆን አለበት። በዚህ መሰረት የኢትዮጵያን የፌደራል አወቃቀር ስናይ ብሄራዊ አንድነትን ሊሰራልን የሚገባውን ፓለቲካዊ ማንነት ለብሄሮች ሰጥቶታል። በሌላ አገላለጽ ፌደራሊዝሙ የመነጨው ከብሄር ፓለቲካ ነው። ኢህአዴግ ግንባር ነው የሚባለው። ውሁድ ፓርቲ ባለመሆኑ ብሄራዊ ማንነትን የሚሰራው በዚሁ የኮንትራት ውል በግንባርነት ተክለ ሰውነቱ ነው። ይህ በመሰረቱ ብሄራዊ ማንነት የሚባለውን ትልቅ የፓለቲካ ጠገግ ውሽልሽል ያደርገዋል። ፌደራሊዝም ሲሰራ ሁለቱንም ማንነቶች እንዲጠብቅ እንጂ ብሄራዊ ማንነትን በግንባር ኮንትራት አውሸልሽሎ ለአካባቢያዊ ማንነት ብቻ ማሰብ የፌደራልን ጽንሰ ሃሳብ ያፈርሳል። በኢትዮጵያ ውስጥ የብሄሮችን ማንነት ለመጠበቅ የሚያስችል የፌደራል ስርአት ዘርግቶ ነገር ግን ፓለቲካዊ ስብእናችንን በአንድ ብሄራዊ ጠገግ ስር ማሳደር ይኖርብናል። የአሁን ዘመን ፌደራሊዝም የወደቀው በተለይ ብሄራዊ ማንነትን መጠበቅ አለመቻሉ ብቻ ሳይሆን የቡድኖችን ማንነት ለመጠበቅም ፍትሃዊ የስልጣን ክፍፍል የለውምና በዚህ በኩልም ጤነኛ ቡድናዊ ማንነትን እንድናዳብር ለማድረግ አላስቻለንም።
ለምሳሌ ስዊዘርላንድን ብናይ በቋንቋ ማህበረሰብ ላይ የተመሰረት ክልል ፈጥራ ስትኖር ፓለቲካዋን ግን በአንድ ብሄራዊ ማንነት ስር ነው መስርታ የምትኖረው። ስዊዘርላንድ ውስጥ በዘር ላይ የተመሰረተ የፓለቲካ ድርጅት ማቆም በህግ ያስቀጣል። ወደ ሃገራችን ኢትዮጵያ ስንመጣ የኢትዮጵያ የክልል አፈጣጠር መስፈርት ምን እንደሆነ መመርመር ተገቢ ነው። የብሄር ፌደራሊዝም ችግሮች አለበት እየተባለ የሚተቸውን ትችት ለጊዜው እንተወውና ለመሆኑ የኢትዮጵያ የፌደራል ስርአት ወጥነት ያለው በብሄር ፌደራሊዝም የሚገለፅስ ነው ወይ? የሚለውን እንድናነሳ ያደርገናል። እንግዲህ ኢትዮጵያ ከ82 በላይ ብሄሮችን ይዛ ዘጠኝ ክልሎችንና ሁለት ልዩ ቻርተር ከተሞችን አዋቅራ ቁጭ ብላለች። ይህን ስናይ 82 ብሄር ያላት ሃገርና የብሄር ፓለቲካን የምታራግብ አገር በዘጠኝ የከፈላትን ምስጢር ለማወቅ ያቋምጠናል። ኢትዮጵያ ፌደራሊዝሟ ግልጽ በሆነ የብሄር ፌደራሊዝም ይገለጽ ዘንድ ሁሉም ብሄሮች የክልል መንግስትነት ስልጣን ሊካፈሉ ይገባ ነበር። አንዱ ብሄር የራሱ ህገ መንግስት ያለው ይሆንና እንዱ ደግሞ የዞንነት ስልጣንን ይጋራል ሌላው ብሄር ደግሞ የልዩ ወረዳ ስልጣን ወደዚያ ይወረወርለታል። እውነተኛ የስልጣን ክፍፍል በሃገሪቱ አለመኖሩ ብቻ ሳይሆን ችግሩ በብሄሮች እኩልነት ዙሪያ የፍልስፍናና የአመለካከት መሰረታዊ ችግር እንዳለም ያሳያል። የብሄሮች እኩልነት መገልጫ እንዱ እኩል የስልጣን መጋራት ነበር። ሎጂኩ እንደዚያ ነው። ማንነትን መሰረት ያደረገ ፌደራል ስርአት ተፈጠረ ከተባለ ግልፅ መሆን አለበት። በቁጥራቸው አናሳ የሆኑትን እያሰባሰቡ አንድ ክልል የማድረግ ጨዋታ ከሆነ ሃረሪ ለምን ክልል ሆነች? ብለው ሰዎች በዚህ የፌደራል ስርአት ግልፅነት ላይ ጥያቄ ያነሳሉ። የሃረሪ ህዝብ ብዛት ከአቃቄ ክፍለ ከተማ ህዝብ ያንሳል፣ ከሲዳማ እጅግ ብዙ እጅ ያንሳል። ቢያንስ ዞን እንኳን አድርጉኝ እያለ ከሚታገለው ከኮንሶ ህዝብ በብዙ እጅ ያንሳል። ግን ክልል ነው። ሃረር ክልል የሆነው ባህሉን እንዲጠብቅ ነው አይባልም መቼም። ሁሉም ቡድኖች የሚኮሩበት ባህል አላቸውና። ሁሉም ቡድኖች የሚጨበጡና የማይጨበጡ ባህሎች አሏቸው። ከዚህም በላይ የማንም ባህል ከማንም አይበልጥምም አያንስምም። የሲዳማ ህዝብ ጥያቄ የግልጽነት ጥያቄ ነበር። ይህ ብሄር በቁጥሩ ከትግራይ ከቤንሻንጉል ከአፋር ከጋምቤላ ህዝብ ሳያንስ ትግራይና እነዚህ የተዘረዘሩት ክልል ሆነው ሲዳማ ክልል መሆን አለመቻሉ ብዙ ሰው እንዳደናገረ ይኖራል። ሃምሳ ስድስት የሚሆኑ የደቡብ ብሄሮች አንድ ክልል ሆነው ሃረሪና አፋር ቤንሻንጉል እንዲሁ ክልል ሆነው ስናይ ፌደራሊዝሙን በብሄር ፌደራሊዝም ለመግለጽም ይቸግረናል። መንግስት የሚለው ሁሉም ብሄሮች የክልልነት ደረጃ ባያገኙም በዞንና በወረዳ ደረጃ የራሳቸውን መንግስት አቁመዋል ነው። ይሄ እንዝህላል መልስ ነው። መንግስት እንደሚለው ፓለቲካው በብሄር ላይ ስለቆመና አስተዳደሩ በጎጥ ስለሆነ የብሄር ፌደራለዝም እንበል ነገር ግን እኩልነት የሌለበት የብሄር ፌደራሊዝም ይባል እንደሆን አላውቅም። ብዙ ብሄሮች የከረረ ጥያቄ የማያነሱት ለስርአቱ እውቅና ካለመስጠት ስሜት ነው እንጂ ፌደራሊዝሙ ይሄ ነው የሚባል ግልጽ ፀባይ (patern) የለውም በውነቱ። ስለሆነም የዚህ የፌደራል ስርአቱ አፈጣጠር ራሱ ችግር አለበት ማለት ነው። መንግስት ብዙ ጊዜ የሚናገረው ቡድኖች ማንነታችውን አግኝተዋል የሚል ነው። የሚገርመው ይህ ስርአት ልዩነትን በማስፋት በአንድ ጽንፍ እየተከሰሰ በሌላ በኩል ደግሞ በግድ የሆነ ምስለትም ይታይበታል። ለምሳሌ የወልቃይትን ህዝብ ጉዳይ ማየት በቂ ነው። ስለዚህ ፌደራሊዝሙ በሁለት በኩል ይታማል። አንደኛው ቡድናዊ ማንነትን ጠብቆ ከብሄራዊነትጋር ሳይጋጭ ለማስኬድ አልቻለም ልዩነትን እያራገበ ዜጎች ከብሄራዊ ማንነት ጋር ያላቸውን መጣበቅ እንዲላላ አድርጓል ግልፅነትና ወጥነት የለውም የሚል ሲሆን በሌላ በኩል ለባህል ምስለት ወይም ለማንነት መጥፋት ያጋለጠው ቡድንም አለ። ለዚህ ዋና መገለጫው የወልቃይት ህዝብ ጉዳይ ነው። ከፍ ሲል እንዳልነው ወልቃይት በሃይል ትግራይን መስሎ እንዲኖር የተፈረደበት ህዝብ ነው። ለዚህም ነው በአሁኑ ወቅት ይህ የወልቃይት ጥያቄ ከፍተኛ ንቅናቄ እያመጣ ያለው። በአጠቃላይ የአቶ መለስ የፌደራል ስርአት ምስለት ፣ ጽንፍ የወጣ ልዩነት፣ ብሄራዊና አካባቢያዊ ማንነቶች የሚጋጩበት፣ ግልጽ ያልሆነ የብሄሮች የስልጣን ክፍፍል በአንድ ጊዜ የሚታይበት አስገራሚ የመንግስት ስርአት ነው። ስለዚህ ፌደራሊዝሙ ማንነቶችን በመንከባከብ ረገድ ችግር የፈጠረ ስርአት ነውና ኢትዮጵያ የፌደራል ስርአት አራምዳለሁ ብትል ስህተት ነው።

ዴሞክራሲ

ሌላው የፌደራል ስርአት እምነት ዴሞክራሲን እንደ ልቡ ለማንሸራሸር የሚያስችል ሲስተም አለው ስለሚባል ነው። አንዱ የፌደራሊዝም ስርአት ጭንቀት ስልጣን ወደ ህዝቡ ጠጋ እንዲልና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንደልብ እንዲሰሩ ነው። በዴሞክራሲ ስርአት ውስጥ የዜጎች የመምረጥ የመመረጥ መብት፣የንብረት ባለቤትነት መብት ጉዳይ፣ የዜግነት መብቶች ጉዳይ በጣም የፌደራል ስርአት የሚጨነቅላቸው ጉዳዮች ናቸው። ኢትዮጵያ የፌደራል ስርአትን ተግባራዊ ለማድረግ ስትነሳ የቡድንንም የግለሰብንም መብት ለመጠበቅ በሚያስችል መሆን አለበት። ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ የብሄር ፌደራሊዝም ካመጣቸው ችግሮች እንዱና ጉልሁ ጉዳይ ግዙፍ የዴሞክራሲ ክፍተት (a huge democratic deficit) ማምጣቱና ለዜጎች የሃገር ባለቤትነት መብት እክል መፍጠሩ ነው። እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ ብሄሮች ተዋልደዋል፣ በተለያየ የሃገሪቱ ክፍል ተበትኖ የሚኖረው ህዝብ ብዙ ነው። ለምሳሌ ያህል በኦሮምያ 11 ሚሊየን አማራዎች ይኖራሉ። በሚሊየን የሚቆጠሩ ኦሮሞዎች በአማራ፣በደቡብ፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ በሃረሪና በሌሎችም ክልሎች ይኖራሉ። ብዙ ጉራጌዎች ከክልላቸው ውጭ ይኖራሉ። የብሄር ፓለቲካ የወለደው ይህ የኢትዮጵያ የፌደራል ስርአት ያመጣው ችግር የነዚህን እጅግ ብዙ ዜጎችን የፓለቲካና የዜግነት መብታቸውን እንዲያጡ አድርጓል። ስለ ህዝብ መብት እጨነቃለሁ የሚለው መንግስት በዚህ የፌደራል ስርአት ለዲሞክራሲያዊ መብት ድርቅ ያጋለጣቸው ዜጎች ብዛት እጅግ አያሌ ነው። በኦሮምያ የሚኖረው አማራ ብቻ በቁጥሩ አሁን ያሉትን የአምስት ክልሎች ህዝብ ማለትም የአፋርን፣የትግራይን፣የሃረሪን፣የቤንሻንጉልን፣የጋምቤላን ህዝብ ተደምሮ ይበልጣል።ይሄ ሁሉ ህዝብ ሲስተሙ በፈጠረው የዴሞክራሲ ክፍተት ብቻ ፓለቲካዊና የዜግነት መብቶቹ በሃይል ይሰበራሉ። ከክልሉ ውጭ የሚኖረው የኦሮሞ ህዝብ ከብዙ የደቡብ ብሄሮች ይበልጣል። እንግዲህ ሲስተሙ የዚህን ሁሉ ህዝብ መሰረታዊ የዴሞክራሲ መብቶች እንዲጣሱ ያደርጋል። አንዱ የኢትዮጵያ የመንግስት ስርአት ትልቅና መሰረታዊ ችግር ይሄ ነው።

የብዙዎችን ትኩረት ወደሚስበው ወደ የሃረሪ ክልል ጉዳይ ልመልሳችሁ። ሃረሪ ክልል የኢትዮጵያ የፌደራል ስርአት የዴሞክራሲን ችግር፣ የግልጽነት ችግር፣ አጠቃላይ የኢትዮጵያን ፌደራል ስርአት ቅጥ ማጣት በተምሳሊት ቁልጭ አድርጋ የምታሳይ ክልል ናት። በዚህ ጉዳይ ላይ ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን በኢትዮጵያ ነገ ፕሮግራም ላይ ዶክተር ሰለሞን ጋሻው ከአቶ ግዛው ለገሰ ጋር ያደረጉት ውይይት እጅግ መሳጭ ነበር። በዚህ ጽሁፍ ውስጥ ተጨማሪ አሳብ መስጠቱን መረጥኩ።

እንግዲህ ሃረሪ የቆዳ ስፋቷ 334 ኪሎ ሜትር ስኩየር ያህል ሲሆን 183,415 የሚሆኑ ወንድና ሴት ኢትዮጵያውያንን ይዛለች። ከአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በህዝብ ብዛት ታንሳለች። ሃረሪ ካሏት ህዝብ መካከል 56.4% ኦሮሞዎች፣ 22.7% አማራዎች፣ 4.3% ጉራጌዎች፣ 1.53 % ትግሬዎች፣ 8.65% ሃረሪዎች፣ 1.26% አርጎባዎች ናቸው:: ይህ ክልል ሲዋቀር ከሃረሪ ከተማ በተጨማሪ አስራ ዘጠኝ ወረዳዎች ከኦሮምያ ተጨምረውበት እንደሆነ በዚህ ዙሪያ ጥናት ያካሄዱ ባለሙያዎች ይገልጻሉ። የኦሮሞው ቁጥር በአንደኛነት የበዛው ከአጠቃላዩ የህዝብ ብዛት ከግማሽ በላይ የሆነው እነዚህ ቀበሌዎች ስለተጨመሩ ነው ማለት ነው። በዚህ ክልል አወቃቀር ጊዜ ምንም ተጠይቅ የማይታይ ብቻም ሳይሆን የሚገርምም ነው። የክልሉ ባለቤት የሆነው 8.65% የሚሆነው ህዝብ ሲሆን 91% በላይ የሆነው ህዝብ የዚህ ክልል ዋና ባለቤት አይደለም። የመገንጠል አሳብ ቢመጣ እነዚህ ወደ ዘጠኝ በመቶ የሚሆኑ ወገኖች ብቻ ናቸው የሚወስኑት ማለት ነው?። ዋና ባለቤት ማለትስ ምን ማለት ነው? ከዘጠና አንድ በመቶ በላይ የሆኑት ኢትዮጵያውያን መንግስት እንደሚለው መጤ ናቸው እንዳይባል ሃረር ላይ የተጨመሩት አስራ ዘጠኝ ቀበሌዎች ከኦሮሞ ክልል በመሆኑ እነዚህ ኦሮሞዎች መጤ አይባሉም ማለት ነው። ምክንያቱም ኦሮሞዎቹ ከተፈጠሩበት ቦታ ከነአፈራቸው ነው ወደ ሃረሪ የተከለሉትና በምን ሂሳብ ኦሮሞዎች በዚህ ክልል ውስጥ እንደመጤ እንደሚታዩ በተለይ ግልጽ አይደለም። በዚህ ክልል ስናይ ዘጠና አንድ በመቶ የሚሆነው ህዝብ የባለቤትነት ስሜት እንዳይኖረው ሲደረግ በአለም ያልታየ ከፍተኛ የዜግነትን መብት የጣሰ ጉዳይ ይሆናል። ይህ ክልል የሚኖረው እነዚህ ዘጠና አንድ በመቶ በሚሆኑ ህዝቦች እውቀት፣ ጉልበት፣ ታክስ ነው። እነዚህ ህዝቦች ባለቤትነት መነፈጋቸው በተለይም ኦሮሞዎቹ በራሳቸው መሬት ላይ እንደ ማይኖሪቲ መታየታቸው የብሄር ጭቆና አይደለም ወይ? “አናሳው” ብዙሃኑን የሚጨቁንበት ስርዓት ተፈጠረ ማለት ነው። ለዚህ ነው የብሄር ፖለቲካ በሁለት አቅጣጫ የተሳለ ሰይፍ አለው የሚያስብለን። በአንድ በኩል አብላጫ ቁጥር ያለው ስልጣን ሲይዝ የማጆሪቲ አምባገነን ሲፈጠር፣ ማይኖሪቲ የበላይ ሲሆን ደግሞ የማይኖሪቲ አምባገነንነትን ስለሚያመጣ ከብሄር ጭቆና ነጻ አያወጣም። ጨቋኝ የነበረውን ተጨቋኝ፣ ተጨቋኝ የነበረውን ጨቋኝ እያደረጉ በበቀል ጎዳና ከመነዳት ይልቅ ለምን ከዚህ አንወጣም?

የፓለቲካ መብትን በሚመለከት የሃረሪን ጉዳይ ስናይ ከፍተኛውን ስልጣን የክልሉ ተወላጆች ሲይዙ ኦሮሞዎችም የክልሉ ተወላጆች ሆነው ሳለ ሁል ጊዜ ሊቀመንበሩ የሃረሪ ሰው እንዲሆን መወሰኑ ምክትሉ የኦሮሞ እንዲሆን መወሰኑ ደግሞ ይገርማል። ሊቀመንበር በመሆን ነው የክልል ባለቤትነት የሚረጋገጠው ማለት ነው? ጋምቤላ ውስጥ እንዴት ነው ሊቀ መንበር የሚኮነው? ቤንሻንጉል ደቡብ ወዘተ. ይህ አካሄድ ምንም መሰረት የሌለው የእንዳወጣው የግብር ይውጣ ስራ ይመስላል። የብሄር ጭቆናን በግልጽ የሚያራምድ ስራ እየተሰራ ያለበት ሁኔታ ላይ ነው ያለው። ይህ ክልል ሲቋቋም በፈቃድ ላይ ስለተመሰረተም አይደለም። የሃረር ህዝብ የታወቀ ነው። የሃረርና የድሬ ህዝብ በእንግዳ ተቀባይነቱ፣ ከሁሉ ጋር በመኖር ችሎታው መላው የኢትዮያ ህዝብ ይመሰክርለታል። ውድ ህዝብ ነው በጣም። እንዲህ አይነት ዘረኝነት ሲያይ አቦ ይሄን ዘረኝነት ወደዚያ ውሰዱልን ነው የሚለው። ተግባሩ ራሱ የሃረርን ህዝብ ባህል ያላገናዘበ የሃረርን ህዝብ እሴቶች የጣሰ ነው።

ሃረር ውስጥ ከዘጠና አንድ በመቶ በላይ የሆነው ህዝብ እየታዘበ የክልሉ ርእሰ መስተዳድር ከሃረሪ ተወላጅ ብቻ ነው ሁለተኛው ከኦሮሞ ነው የሚለው ህግ ከየት ነው የሚመጣው? የ“ማይኖሪቲ” ሩል አሰራርን በማምጣትና የብዙሃኑን የፖለቲካ ተሳትፎ በመገደብ ፍትህ ተበየነ ማለት ነው ወይ? በሌላ በኩል ያለው አስገራሚ ጥያቄ ደግሞ እነዚህ “መጤ” የሚባሉት በየክልሉ ያሉ ኢትዮጵያውያን በአሜሪካንና በአንዳንድ አገሮች እንደሚባለው ህገ-ወጥ መጤዎች (Illegal immigrants or undocumented immigrants) መሆናቸው ይሆን? ይገርማል መቼም:: እነዚህ ስደተኞች አንዳንዶቹ በ18ኛው ክፍለ ዘመን አያቶቻቸው ወደዚያ የሄዱ ናቸው። እነዚህ የልጅ ልጆች መቼ ነው በክልሉ መንግስት የክልል ዜግነት ወይም ሌላ ዶክመንት ካለ ተሰጥተው ሙሉ የፖለቲካ ተሳትፎ የሚኖራቸውና የክልሉ ተወላጆች ወይም የክልል ዜግነት ካለ የክልሉ ዜጎች የሚባሉት? በክልሉ ውስጥ የተወለዱት የክልሉ ተወላጅ ስለምን አይባሉም? አንድ ህዝብ በአንድ መሬት ላይ ሌላው ይቅርና የመቶ አመት እድሜ ካለው በቃ አገሩ እኮ ነው። የዚያ ዜጋ የዚያ ሃገር ባለቤት ይሆናል። ፈልሳችሁ ነው የሚባል ነገር ከሰው ልጆች ታሪክ ጋር አይሄድም። ኢትዮጵያ ራሷ የተፈጠረችው በኦሮሞ መስፋፋት፣ በአማራ መስፋፋት፣ በደቡብ ህዝቦች መስፋፋት በሁሉም ህዝቦች ንቅናቄ ነው። የጊዜው ርዝማኔ ይለያይ እንጂ ሁሉም ብሄሮች ከዚህ ነው የመጣነው፣ ከዚያ አገር ነው የመጣነው የሚል አፈ ታሪክና የተጻፈ ታሪክ ይኖራቸዋል። መሬትን በእጁ ጠፍጥፎ የሰራ የለምና ሰዎች ተነቃንቀው ለረጅም ጊዜ ከኖሩ በኋላ በዚህ በሰለጠነው ዓለም ጊዜ እንዲህ ዓይነት አሰራር ማምጣት በዓለም አልታየም። በተለይ በተለይ አንድ ሰው የተወለደበት አገር አገሩ መሆን አለበት። ያ የተወለደበት አገር አገሩ የማይሆንበት ምንም ምክንያት የለም። ተወልዶ ያደገበትን ምድር የመንከባከብ የመግዛት ችሎታ አለው። ይሄ ግልጽ ሎጂክ ነው። በአሜሪካ ህግ አንድ ሰው በአሜሪካ የአየር ክልል ውስጥ በአውሮፕላን ሲሄድ ቢወለድም እንኳን ዜግነት የማግኘት መብት አለው። አሜሪካ አገሩ፣ የዚህ ዓለም እጣ ፈንታው ትሆናለች። ይሄ ትክክለኛ ጥርት ያለ ሎጂክ ነው። የኢትዮጵያ ፌደራሊዝም ግን ይህን የዴሞክራሲ መብት አፈር አብልቶታል።

ሌላው መሳጭ ጉዳይ ደግሞ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጉዳይ ነው። ቤንሻንጉል ጉሙዝ እንደ ክልል የተፈጠረው ከቀድሞው ምእራብ ጎጃም እና ከሰሜን ምስራቅ ወለጋ ክፍለ ሃገራት ነው። ይህ ክልል በሶስት ዞኖችና በሃያ አንድ ወረዳዎች የተዋቀረ ሲሆን 50,699 ስኩየር ኪሎ ሜትር የቆዳ ስፋት አለው። 784,345 ህዝብ ይዟል። የህዝብ ብዛት ደንሲቲው ደግሞ 15/Km2 ያህል ነው። በዚህ ክልል ውስጥ ብዙ ቡድኖች የሚኖሩበት ሲሆን ከአጠቃላይ ህዝቡ ውስጥ 25.41% በርታ፣ 21.69% አማራ፣ 20.88% ጉሙዝ፣ 17.69% ኦሮሞ 7.73% ሺናሻ 4.01% አውንጊ፣ ናቸው። ይሁን እንጂ ይህ ክልል በዋናነት በባለቤትነት የተሰጠው ለበርታና ለጉሙዝ ነው። ሌሎቹ በተለይም ኦሮሞና አማራ እንደ መጤ እንዲታዩ ይደረጋል። ስያሜውን ስናይ በሁለቱ ስም ነው የሚጠራው። ደቡብ ውስጥ ብዙ ስለሆኑ የደቡብ ብሄር ብሄረሰብና ህዝቦች እንደተባለው ሁሉ ካንድ በላይ ብሄር ያላቸውን በሆነ ስያሜ አስገብቶ የጋራ መሆኑ እዘህ ክልል ላይ ደግሞ አይሰራም። ለመሆኑ ግን ይህ ክልል የተወላጁ ነው ስንል ምን መረጃ ይዘን እንደሆነ ባይታወቅም እዚህ ቤንሻንጉል ውስጥ በተለይም ሁለቱ ዋና ባለቤቶች ማለትም ጉሙዝና በርታ ዴሞክራሲን ለማስተናገድ ሲሞክሩ የማጆሪቲ ሩልን ጉዳይ የግድ ከቡድኑ ብዛት ጋር ሊያያይዙ ነው ማለት ነው። ሃረር ውስጥ ማይኖሪቲው በመጤው ላይ የፖለቲካ የበላይነት እንዲኖረው ሲደረግ ቤንሻንጉል ደግሞ አቶ መለስ ራሳቸው በፈጠሩት ክልል “ከዋናዎቹ” ብሄሮች ብዛት ያለው የበላይነቱን ይዞ ይኖራል ማለት ነው። በዚህ የብሄሮች ፍትህ ተበየነ ማለት ነው?

አንድ ክልል ጋምቤላም ይሁን፣ ኦሮምያ ወይም ሌላ ክልል ይህ ክልል የተወላጆቹ ነው ከተባለ ኢትዮጵያዊነት የማይጨበጥ አሳብ ብቻ ይሆናል ማለት ነው። ኢትዮጵያዊነት መሬት የለውም ማለት ነው። ዜግነት መሬት የለውም። ይህ ግዙፍ ሃብት በዚህ በብሄር ፖለቲካና በብሄር ፌደራሊዝም ጊዜ ዋጋ ያጣል። ኢትዮጵያዊነት ማለት በኢትዮጵያዊነት በዜግነት ከኢትዮጵያ የምናገኘው የፖለቲካና የመሬት ባለቤትነትን የሚያሳይ ነው። ዜጎች በሄዱበት ቦታ በአራቱም ማእዘናት የመኖር የመስራት በሃገራቸው ፖለቲካ ላይ የመሳተፍ መብት አላቸው። ይህ መብት የሚዘረዘረው በኢትዮጵያዊነት በዜግነት መብት መከበር በሚጀምርበት ጊዜ ነው። ቤንሻንጉል ጉምዝ ውስጥ ተደምረው ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ኢትዮጵያውያን የፖለቲካ ተሳትፎአቸው ይገደባል። ምክንያቱ ደግሞ የዛሬ መቶ ሁለት መቶ አመት ሊሆን ይችላል አባትህ ከኦሮሞ ወይም ከአማራ ወይም ከደቡብ አለያም ከትግሬ መጣ በማለት ነው። ይሄ በዓለም ያልታየ ታሪክ ይመስለኛል። ከፍ ሲል እንዳልነው ዓለም በንቅናቄ ነው የተፈጠረችው። የትም አለም የሰው ልጆች ተነቃንቀዋል። አሁን በዚህ ዘመን ነው አንጻራዊ ርጋታ ያለው። ያም ሆኖ ግን እስካሁን በዓለም ላይ ወደ 200 አገራት የድንበር ክለላ ጣጣ ያልጨረሱና በተለያየ ደረጃ ግጭቶች ያሉባቸው ናቸው።

ከተባበረችው አሜሪካ ብዙ ልንማር የሚገባ ይመስለኛል። አንድ የማውቀው ሰው እድሜው ከሰላሳ በላይ የሆነ ዲቪ ደርሶት ሄደ። በዚያ ጥቂት አመታት ቆይቶ እነሆ ዛሬ ዜጋ ነው። የወለዳቸው ልጆችና እሱ በስተርጅና ያገኘው ዜግነት ሙሉ ፓለቲካዊና ማህበራዊ መብትን ሰጥቶታል። በቃ አሜሪካ ውስጥ የፈለገበት ስቴት ሄዶ ቢኖር መብቱ አይሸራረፍም። በእንዲህ አይነት አለም ላይ እየኖርን ቅም አያቱ ከጎንደር የመጡ ናቸውና ቤንሻንጉል የሱ ክልል አይደለም የሚባል ነገር አይሰራም። ጎንደር በሃገሩ የመንቀሳቀስ መብት አለውና።

በዓጼ ምኒሊክ ዘመን ዓለም በንቅናቄ ላይ ነበረች። የተሰሩ በደሎች የሉም አይደለም። በሚገባ አሉ። በጦርነት የተጎዱ፣ የተፈናቀሉ ብዙ በደሎች አሉ። ዓለም እንደሆነ ሆነናል። ይህን ታሪክ የምናድሰው የዛሬ አምሳ አመት መቶ አመት መፈናቀል ነበር ብለን ከዚያ እኛው ክልል ፈጥረን አንተ ከዚህ ክልል ፈልሰሃል ይሄ ክልል የእንትናና የእንትና ብቻ ነው ለማለት ምን ችሎታ አለን? ለምን ለሁሉም የሚሆን ሁሉን ነጻ የሚያወጣ መፍትሄ አናመጣም። ራሳችን እንዳሻን ክልል ፈጥረን ሰዎችን ማፈናቀል የለብንም። ኢትዮጵያ ስትፈጠር ዘጠኝ ክልል ነበረች የሚል ታሪክ የለም። ይህን ዘጠኝ ክልል የፈጠሩት አቶ መለስ ናቸው። እሳቸው በፈጠሩት ክልል ውስጥ እከሌ መጤ እከሌ ነባር ለማለት ችሎታው የላቸውም። አቶ መለስ ኢትዮጵያን በዘጠኝ ከከፈሉ በሁዋላ የደቡብ ብሄሮች የክልልነት ጥያቄ ሲያቀርቡ ክልል አለቀ አሁን ወደ ልማት ነው ብለው መለሷቸው።

ቤንሻጉል ውስጥ ያሉ ሁሉቱ ገናና ቡድኖች ማለትም በርታና ጉሙዝን የፖለቲካ ሽኩቻ ውስጥ የከተታቸው የፖለቲካው አባዜ ነው። ጉምዞች በርታ ተጭኖናል የሚሉት በቁጥሩ ስለበዛና ማጆሪቲውን ስለያዘው ነው። ጉምዞች እልህ ውስጥ ከገቡና ማጆሪቲ መሆን ካማራቸው ምንድን ነው መፍትሄው? ቶሎ ቶሎ መዋለድ ነው ማለት ነው። ለምን ወገኖቻችን የፖለቲካን ጥበብ ከዚህ ከዚህ ጋር እንዲያያይዙ እናደርጋለን። ለምን ፍትህን መርህን እንዲመረኮዙ አናደርግም የሚለው ጥያቄ ዛሬስ በመረረ ሁኔታ መነሳት አለበት።

ጋምቤላም ብንሄድ እንደዚሁ ነው። ጋምቤላ ውስጥ ወደ አምስት የሚሆኑ ብሄሮች የጋምቤላ ክልል ባለቤቶች ናቸው ይባላል። ከነዚህ ውጭ ያሉት ቡድኖች መጤዎች (illegal immigrants) ናቸው። ከፍ ሲል እንዳልነው ላለፈው መቶ አመት በላይ ህገ ወጥ ሆነው የኖሩ ናቸው ማለት ነው። ጋምቤላን በባለቤትነት ከሚያስተዳድሩ አምስት ዋናዋና ብሄሮች መካከል ሁለቱ ማለትም የኑየር ብሄርና የአኙዋክ ብሄር መካከል የሚታይ የሃይል ሽኩቻ የመነጨው ከዚያው ከብሄር ፖለቲካ ነው። አንድ ነገር ልብ ማለት ያለብን እነዚህ ቡድኖችም ይሁኑ በየትኛውም የሃገሪቱ ክፍል የሚነሱ የብሄር ግጭቶች ቡድኖች አብረው ለመኖር ካለመፈለግ ወይም አብሮ መኖር እንግዳ ስለሆነባቸው አይደለም። እንግዳ ሆኖ የሚያጋጫቸው የጎሳ ፖለቲካና በውስጡ የያዘው እምቅ ግጭቶች ናቸው። ከዚያ በተረፈ የቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ የጋምቤላ፣ የሃረሪ፣ የደቡብ፣ የአማራ ወዘተ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር በመኖር አይጋጩም። ኢትዮጵያዊ ሁሉ ደግየ ህዝብ ነው።
ብሄር ተኮር ግጭቶች በዚህ ዘመን በጣም ከፍ ያሉ ሲሆን አብዛኛው በመንግስት በምስጢር ስለሚያዝ መረጀ ይጠፋል እንጂ ከፍተኛ የሆነ የብሄር ፖለቲካ የወለደው ፌደራሊዝም ብዙዎችን አሳጥቶናል ሰላም ነስቶናል።

ግን ግን…..ከሰባዊ መብት አኳያስ እነዚህ ሰዎች የት ይሂዱ? እስከ መቼስ ነው የክልሉ ተወላጅ የሚባባሉት የሚለው ጥያቄ ትልቅ የሰብአዊ መብት ጥያቄ ነው።ሌላው ይሄ የብሄር ፓለቲካ የወለደው የብሄር ፌደራሊዝም በዜጎች የሃገር ባለቤትነት ላይ ችግር ሲፈጥር የዚህ ችግር ዋና ተጋላጭ የሆነው ማህበረሰብ ከሁለትና በላይ ብሄሮች የተወለደው ቅይጡ ኢትዮጵያዊ ነው። ይህ ዜጋ በህወሃት ጊዜ የተሰጠው እድል ወይ እናቱን ወይ አባቱን እንዲመርጥ ነው። ይሄ ደግሞ ሳይንስ የጎደለው ተራ ነገር ነው በውነት። አንድን ዜጋ ከናትህና ከአባትህ ምረጥና የአንድ ብሄር አባል ሁን ሲባል ይህ ሰው ሁለቱንም ይወዳል። ከሁለቱም የወራሽነት ሙሉ መብት አለው። ሁለቱንም ማስከፋት አይፈልግም። የሚገርመው ይህ ህዝብ በቁጥሩ ደግሞ ከኦሮሞና አማራ ቀጥሎ የሚሰለፍ ነው።ግዙፍ ህዝብ ነው ለዴሞክራሰያዊ መብት ድርቅ የተጋለጠው። በአንድ የደቡብ ክልል ውስጥ ያየሁት ነገር እስካሁን ይገርመኛል። የወረዳው ምክር ቤት ጸሃፊ ከሁለት የተለያዩ ብሄሮች የተወለደ ነው። ይህ ሰው አንዱን መርጦ የመጣ ነው ማለት ነው። የሚገርመው ይህን ስልጣን ይያዝ እንጂ ተሰሚነቱ ግን ዝቅ ያለ ነበር። እሱ የወሰነውን የሴክተር ሃላፊው ይሽረዋል። እሱም ይህን ተረድቶ በዘያው በግማሽ መብቱ ይኖራል። ጎበዝ ቢሆንም ተሰሚነቱ ግን በዚህ በዘሩ ምክንያት ቀንሷል። የዚህን ባለስልጣን ምሳሌ ሳነሳ ከኦሮሞና አማራ የተወለዱት፣ ከጉራጌና ወላይታ የተወልዱት ወዘተ በአጋጣሚ ወደ ስልጣን ሲመጡ ባሉባቸው ክልሎች ተሰሚነታቸው እንደ ሌሎቹ የብሄሩ አባላት አለመሆኑን ማሳያ ስለሚሆን ነው። ሌላው አስገራሚ ነገር ደግሞ በዚያ ወረዳ ውስጥ ያሉ በተለይ የሰሜን ተወላጆች ያንን የሃገራቸውን ክፍል በፓለቲካ ተሳትፎ የማገልገል አሳቡም የላቸውም። የሚያስጠጋቸው የለምና። የኢትዮጵያ የፓለቲካ መብት ወንዝ አትሻገርም። በዚህ ወረዳ ይኖሩ የነበሩ የሌላ ክልል ዜጎች እንደ ውጭ ዜጋ ይታያሉ። ህዝቡ ነው እንጂ ጥሩው አስተዳደሩ ባይተዋር ያደርጋል። በዚያ ወረዳ ውስጥ በተለይ ከመሃል አገር የመጡ የጤና ባለሙያዎች የግብርና ሰራተኞችና አስተማሪዎች ራሳቸውን የሚያዩት ልክ የአእምሮ ሃብታቸውን ሸጠው የግል ህይወታቸውን ለመምራት የመጡበት ክልል እንጅ የእናት አገር ስሜት እንዳያዳብሩ የተደረጉ ይመስላሉ።

ሌላው በዚህ የፌደራል ስርአት ለዴሞክራሰያዊ መብቶች እጥረት የተጋለጠው የህብረተሰብ ክፍል ደግሞ ብሄሩን በትክክል የማያውቅና የየትኛውም ብሄር አባል ነኝ ሲል ምቾት የማይሰማው ዜጋ ነው። ይህም በቁጥሩ ቀላል አይደለም። ይህን ሁሉ ህዝብ እየጎዳ ያለ ስርአት ነው።

አስተዳደራዊ አመቺነትና እድገት

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ የፌደራል አወቃቀር ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት አይጠቅምም። አስተዳደራዊ አመቺነት በክልል ምስረታው ወቅት ቦታ ስላልነበረው ተያይዞ ለማደግ የሚመች አይደለም። ከክልል ቅንጅት የክልል ግጭት ሊያይል ይችላል። ያለንን ውሱን የተማረ ሃይል በቅጡ እንዳንጠቀም ያደርጋል። ይሄ ደግሞ ትልቅ ሁለንተናዊ የሆነ ችግርን ያመጣል። በእውቀት ላይ ተመስርተው ሊሰሩ የሚገባቸው ጉዳዮች ሳይሰሩ ይቀራሉ፣ የሃገር ሃብት ያለ ብልሃት ይባክናልና በኢኮኖሚ እድገታችን ዙሪያ አሉታዊ ተጽእኖ ይኖረዋል። በአንዳንድ ከፍተኛ የልማት ስራዎች ላይ ፌደራል መንግስት በአንዳንድ ክልሎች ሊሰራ በሚያስባቸው ፕሮጀክቶች ላይ ከአራቱም አቅጣጫ የሚገኘው ድጋፍ አመርቂ አይሆንም።

በክልሎች መካከል ያለው ዲሞግራፊና ደንሲቲ እጅግ የተራራቀ በመሆኑ ያለንን የተፈጥሮ ሃብት ፍትሓዊ በሆነ መንገድ እንዳንጠቀም ስለሚያደርግ የኢኮኖሚ እድገታችንን ይገታዋል። የኢትዮጵያ የድህነት ችግር ማህበራዊ ችግር በመሆኑ ከፍተኛ የሆነ የኮሚኒቲ ልማት ስራዎችን መስራት ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ ጠንካራ የቅስቀሳ ስራና የብሄራዊነት ስሜት ያሻል። ከሰማኒያ በላይ የሚሆኑ ባህላዊ ቡድኖችን እንዳወጣው በዘጠኝ ከፍሎ ደግሞ በላዩ ላይ የብሄር ፖለቲካን ቸልሶ መኖር ልማትን አያፋጥንም። ከፍ ሲል ያልነውን ምሳሌ ማንሳት በቂ ነው። በሃረሪ ውስጥ የሚኖሩ ከዘጠና አንድ በመቶ የሚበልጡ ኢትዮጵያውያን መጤዎች ከሆኑ እንዴት ብለው ነው ለዘላቂና ለልጅ ልጅ የሚሆን ስራ ለመስራት የሚፈልጉት። ጋምቤላ፣ ቤንሻንጉል፣ አፋር፣ ኦሮሚያና ሌሎችም ክልሎች ውስጥ ያሉ መጤ የተባሉ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ኢትዮጵያውያን ሃብት ለማፍራትና የመጨረሻ ሃይላቸውን አሟጠው በኮሚኒቲ ልማት ስራ ላይ ለመሳተፍ አያስችላቸውም። አካባቢን ለመቀየር አዋጅ ያስፈልጋል። ለአካባቢ ለውጥ ትልቅ የኮሙኒቲ ንቅናቄ (Community mobilization) ስራም ያስፈልጋል። እነዚህ ጉዳዮች ደግሞ ሃይል የሚሆናቸው ብሄራዊ ስሜት ሲገንን ነው። ምንም የማያስገኝ፣ መሬት እንኳን የሌለውን ኢትዮጵያዊነት ይዘው ሃይላቸውን አሟጠው ዜጎች አይሰሩም።

በሌላ በኩል ፌደራሊዝሙ ለዜጎች ፍትህን ለማገልገል ችግር ሆኖ ያታያል። አንድ የመርሃ ቤቴ ሰው ወደ ክልል የሚያደርስ የፍትህ ጉዳይ ወይም የአገልግሎት ጉዳይ ቢገጥመው አዲስ አበባን አቋርጦ ረጅም ጉዞ ተጉዞ ነው ባህዳር የሚመጣው። ደቡብና ኦሮሚያ አንዳንድ ቦታዎችም ላይ ይሄ ችግር አለ። ቅርባቸው ያለውን አዋሳን ጥለው ናዝሬት ድረስ መሄድ ያለባቸው ኦሮሞዎች አሉ። የኦሮሚያ አቀማመጥ ግዙፍ በመሆኑ ለዜጎች አስቸጋሪ ነው። ከአንፊሎ ምእራብ ወለጋ እስከ አዳማ ድረስ ምን ያህል ይርቃል። ከቦረና ተልተሌ ተንስቶ ስንት አገር አቋርጦ አዳማ ለመድረስ ምን ያህል ገንዘብ ይፈጃል፣ ምን ያህል ያደክማል። የፌደራል ስርዓት አንዱ ትልቁ ጥቅሙ ስልጣንን በማውረድ ለዜጎች ፍትህን ማደል ነው። ኦሮሚያ አንድ ክልል ሆኖ የሃገሪቱን አንድ ሶስተኛ መሬት ይዞ ይገኛል። አንድ የሃረሪ ሰው ደግሞ ክልል ቢሮ ለመሄድ በእግሩ ትንሽ ሰዓት ብቻ ይፈጅበታል። አማራ ክልል ውስጥ ያሉ የመርሃ ቤቴና የመንዝ አስተዳዳሪዎች ለስራና ስብሰባ ባህርዳር የውሃ መንገድ ናት። ወጪው ስንት ነው? ……………….ውጥንቅጡ የወጣ የፌደራል ስርአት።

ማጠቃለሊያ
እውነቱን ለመናገር የኢትዮጵያን የፌደራል ስርአት መግለፅ ይከብዳል። ክልል አፈጣጠሩ አንድ ትግራይን በኢኮኖሚ የተሻለች ለማድረግ የተጨነቀ ብቻ ይመስላል። አልፎ አልፎም ተንኮሎችም ያሉት ይመስላል። ለምሳሌ ያህል በአማራ ክልል የኦሮምያ ዞን የሚባል አለ። ወልቃይት ግን በትግራይ ክልል የአማራ ዞን አልተባለም። ህወሃት ይህንን የኔ የሚለውን ክልል ለመጥቀም ሲል በሃገሪቱ ፓለቲካ ውስጥ ልዩነትን፣ ምስለትን፣ የብሄር ፓለቲካን የግለሰብ መብት መደምሰሰን በአንድ ጊዜ በአንድ ዘመን እንዲፈፀሙ አድርጓል። ትግራይ ላይ የተጨነቀውን ያህል ለሌሎች ክልሎች ደንታ የለውም። የዚህ ችግር ክፋቱ ተፅእኖው ከባድ መሆኑ ነው። የሃገሪቱን ህልውና ሳይቀር አደጋ ላይ የጣለ ነው።

አሁን ያለው የፌደራል ስርአት የፌደራል ስርአት አይባልም ምክንያቱም የፌደራል ስርአት ባህርያት የሉትም ብለናል። እንዲህ ሲባል ታዲያ ምን አይነት ስርአት እየተከተልን ነው ስርአቱ በምን ይገለፃል የሚል ጥያቄ ይነሳል። ከፍ ሲል እንደተገለፀው ስርአቱን በሚገባ ለመግለጽ ቢከብድም ከስልጣን ባህርዩ አንፃር ይገለፅ ከተባለ አሃዳዊ አምባገነን አይነት ሲሆን ጎጠኛ ኦሊጋርኬም ነው። ኢትዮጵያ የፌደራል ስርአትን ከነ ሙሉ ክብሩ ልትጠቀም የቻለች አገር አይደለችም። ያሳዝናል። ብዙህ በሆኑ ሃገራት ውስጥ ፌደፍራሊዝም የሚመረጥበት አንዱ ዋና ነገር ግጭትን ቀንሶ ሰላምን ለማስፈን ነበር። በኢትዮጵያ ውስጥ ይህ የፌደራል ስርአት ከተጀመረ ወዲህ የብሄር ግጭቶች ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ይታያል። ይህ የሆነበት ምክንያት እውነተኛ ፌደራሊዝም ስለሌለ ነው። ስልጣን በሃይል ስለተማከለና ስልጣኑ ደግሞ ጎጥን መከታ ስላደረገ ነው።

በርግጥ ለአዲሲቱ ኢትዮጵያችን ተመራጭ የሚሆነው ስርአት የፌደራል ስርአት ነው። ይህ የፌደራል ስርአት ታዲያ ማንነቶችን ማለትም ብሄራዊ ማንነትንና ባህላዊ ማንነትን አጣጥሞ የሚሄድ መሄን አለበት። ለአስተዳደር አመቺ፣ ለጋራ እድገት አመቺ መሆን አለበት። እንዳንድ ወገኖች ፌደራሊዝም ካሉት ችግሮች አንዱ ብሄራዊ ስሜት እየጎዳ አካባቢያዊ ስሜትን ያሳድጋል የሚል ነው። አይመስለኝም። በርግጥ ይህ ችግር ሊከሰት የሚችለው ክልሉ ብሄርን ብቻ መሰረት ካደረገና የብሄር ፓለቲካ ካለ ነው። ሰኪዩላር በሆነ የፌደራል ስርአት ውስጥ ይህ ችግር አይከሰትም። እንዴውም ዜጎች ፓለቲካዊ በሆነ መንገድ በእለት ከእለት ኑሯቸው ሁለት መንግስታትን አያሰቡ የሚኖሩ አይመስለኝም። ለምሳሌ አሜሪካ ወይም አውስትሬሊያ ወይም ካናዳውያን የትም ስቴት ቢሄዱ ባይተዋርነት አይሰማቸውም። የእኔ ባለቤት አሜሪካዊት ስትሆን በምንም አይነት ፓለቲካዊ የሆነ የብሄራዊና የአካባቢያዊ ማንነት ሽሚያ አላይባትም። ያደገችበትን ቀየ እንደማንም ሰው ስትናፍቅ ከማየቴ ውጭ ብሄራዊ ማንነቷና የክልል ስሜቷ ሳይጋጩ አድጋለች። በአንፃሩ እኔ ብሄራዊ ማንነቴን ከክልላዊ ማንነቴ ጋር እንዳይጋጭ ስታገል አገኘዋለሁ። ወያኔ የፈጠረውን የብሄር ፌደራሊዝም እምቢ እያልኩ ፓለቲካዊና ባህላዊ ማንነቴን በተለያየ ሲስተም ለማሳደር አሳብ ለማፍለቅ እታገላለሁ።

በመሰረቱ ፌደራሊዝምን ወደ ኢትዮጵያ ልናመጣ ስናስብ እኛ ኢትዮጵያውያን መጠንቀቅ ያለብን የምንዘረዝረው መንግስት የብሄራዊ መንግስት ክፋይ መሆን የሚኖርበት ሲሆን ፌደራሊዝሙን የባህል ቡድነኝነት መከለያ ካደረግነው ብዙ እምቅ ግጭቶችን ያመጣብናል። በመሆኑም የሚሻለው ሁለት አይነት የፌደራል ስርአት መፍጠር ነው። አንዱ የባህል ፌደሬሽን ሲሄን ይህም ባህልን የሚንከባከብ ሃሳባዊ የፌደራል ስርአት ሲሆን ሌላው ለአስተዳደር፣ለዴሞክራሲ ለልማት ምቹ የሆነ የፌደራል ስርአት እንደገና ማዋቀር ነው። ፓለቲካችንን ከማንነት ፓለቲካ አፅድተን ሳይንሳዊ ፌደራል ስርአት መዘርጋት እንችላለን። ባህላችንን በባህል ፌደሬሽን መካደም ይቻላል። ይህ አሰራር ለኢኮኖሚ እድገትም ከፍተኛ አስተዋፃ አለው።

ለዚህ ሁሉ ግን አገራችን ወደ አዲስ የቡድኖች ኪዳን መግባት ይኖርባታል። ይህ የቡድኖች ኪዳን የኢትዮጵያን ማህበረ ፓለቲካ እስተካክሎ ይሰራልናል። ኢትዮጵያ አዲስ ኪዳን ትገባ ዘንድ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ሊነሳ ይገባል። ስለዚህ አዲስ ኪዳን ስለምለው ጉዳይ ሌሎች ፅሁፎችን እፅፋለሁ። ለዛሬ በዚሁ ላብቃ።

እግዚአብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ
አስተያየት ጥሩ ነው

Advertisements