አስቸኳይ ወቅታዊ መልእክት! ነፃነት ዘለቀ


unity-150x150አሁን ያለንበት ወቅት ለወሬና ለፍልስፍና አመቺ አይደለም፡፡ በሞቀንና በበረደን ቁጥር ከያለንበት ሸጥና ጎጥ እየተነሣን በብዕርም ይሁን በአንደበት የምንወራከብበት ወይም እንካስላንትያ የምንገጥመት ወቅት ላይ አይደለንም፡፡ ጊዜው የጣር መጨረሻ ነው፤ ዘመኑ የነፃነት ትግል ወቅት ነው፡፡ ስለሆነም ከሚያናቁረን ይልቅ የሚያስማማንን ንግግርና ሃሳብ የምንወረውርበት ሊሆን ይገባል፡፡ ከእልህና ከስድብ ይልቅ መቻቻልና መግባባት የሠፈነበት የመጨረሻ ምዕራፍ ሊሆን ጊዜው ግድ ይለናል፡፡

ከቅርብ ወራት ወዲህ የሕዝብ ትግል እየተጋጋለና በስፋትም በጥልቀትም እየጋመ የመጣበት ሁኔታ በግልጽ እየታዬ ነው፡፡ የዘመናት የተናጠል ወያኔያዊ ግፍና በደል የፈጠረውን ይህን አጋጣሚ አለመጠቀም ምን ማለት እንደሆነ ሁላችንም ልናውቀው ይገባል፡፡ ወደሚያስማሙን ነገሮች ይልቅ ወደሚያቆራቁሱን ነገሮች የሚያዘነብል ማናቸውንም ዓይነት ተፃራሪ ሃሳብና አሠራር መቀበል የለብንም፡፡ የተበዳደልን እንኳን ብንሆን፣ የተቀያየምን እንኳን ብንሆን የግል ቂማችንንና ከሀገር ኅልውና አኳያ ተራ ሊባል የሚችል የግል ቁርሾኣችንን አስወግደን ለጋራ ሀገራዊ ነፃነት በጋራ መሰለፍ ይገባናል፡፡ የማይደገምን አጋጣሚ ለበጎ ነገር መጠቀም ተገቢ ነው፡፡ ጅልነት ይብቃ፡፡

እስካሁን በከንቱ ያጠፋነው ጊዜና ኃይል በቁጭት ሊያንገበግበን ሲገባ ለተጨማሪ የርስ በርስ መጋጋጥ አንቸኩል፡፡ ወደራሳችን እንመለስ፡፡ በዘርና በጎሣ፣ በሃይማኖትና በቋንቋ እየተናከስን ወያኔዎች በቀደዱልን ፈር ስንተም እነሆ 25 ዓመታትን ዘለቅን፡፡ በዚህ ሂደት እነሱ እንጂ እኛ የተጠቀምነው ነገር ምንም የለም፡፡ በነዚህ ቀጣፊዎች ተበልጠን ለአገዛዛቸው ብዙ አስተዋፅዖ አደረግን፡፡ ለነሱ ዕድሜ መራዘም እነሱ ካደረጉት ይልቅ እኛ ያገዝናቸው በእጅጉ ይበልጣል፡፡ “እንትና ጨቁኖሃልና በለው!” ስንባል ግር ብለን በመታዘዝ ብዙ ጥፋት አድርሰናል፤ ሊያውም እነሱ ራሳቸው በሞኝነታችን እስኪስቁና ቀሪው ዓለም ጉድ እያለ እስኪታዘበን ድረስ፡፡ “የእነእንትና ሃይማኖት እንዲህ ያለ መንግሥት ሊያቆምብህ ነው” ስንባል ውሸት ይሁን እውነት ከሁለተኛና ሦስተኛ ወገን ሳናጣራ በጭፍን በመቀበል ከወንድሞቻችን ጋር ጥላቻና ቂም በቀል አትርፈናል፤ አንዳችን አንዳችንን በጥርጣሬ ዐይን እንድናይም ተገደናል፡፡ ተዘርዝርሮ በማያልቅ የቆረጣ ሥልት እየተመታን ከሰውነት በታች ሆነን እንድንቀር ተደርገናል፤ ለዚህ ሁሉ ተጠያቂ ወያኔ ብቻ ሣይሆን ራሳችንም ነን፡፡

እስካሁን የነበረን አካሄድ አስቂኝና አስገራሚ ነበር – እንደጭፍግ(ትራጄዲ) ቲያትርም ሊታይ ይችላል፡፡ የአንዲት ሀገር ልጆች መሆናችንን ረስተን ነበር፡፡ የጋራ ዕጣ ፋንታ ያለን መሆናችንን ዘንግተን ነበር፡፡ አንዳችንን የሚያጠፋ ኃይል ሌላኛችንን የሚምረን ይመስለን ነበር፡፡ የሚያጣሉና የሚያጋጩን ለኛው ብለውና ከአንጀት ተቆርቁረውልን ይመስለን ነበር፡፡ በዘርና በጎሣ ሲከፋፍሉን፣ በሃይማኖትና በዘውግ ለያይተው ሲያራኩቱን ለኛ ብለውና አዝነውልን ይመስለን ነበር፡፡ ከ25 ዓመታት የጅልነትና የቂልነት ቆይታ በኋላ ግን እውነቱ የተገለጠልን ይመስላል፡፡

የወለጋ ሕዝብ በወያኔ ላይ ሲያምፅ ለጎንደሩ ምንም የማይመስለው ጊዜ ነበር፤ የሸዋው ሕዝብ በዘረኛው አገዛዝ ላይ ሲያምፅ ለሲዳሞው ምንም የማይመስለው ወቅት ነበር፡፡ በሴቶች ላይ መቅሰፍት ቢታወጅ ወንዶች ምንም ላይመስላቸው የሚችልበት ጊዜ ነበር፡፡ “ክርስትናን አጠፋን!” ተብሎ ሲፎከር ይህ ፉከራ ወደ እስልምናም ሊዛመት እንደሚችል የሚጠረጥር ሙስሊም አልነበረም፡፡ የአዲስ አበባ መሬት ከኗሪው እየተቀማ ለሀብታም ሲቸበቸብ የናዝሬትና የደብረ ብርሃን ነዋሪዎች ነገሬ ሳይሉት እንደሙዚቃ ያዳምጡት ነበር፡፡ ኦሮሞው ከይዞታው የመፈናቀሉ ዜና ለዐማራው የአውሮፓ ዜና ያህል ይሰማው ነበር፡፡ አንዳችም ነገር ሊጎድልበት የማይጠበቅበት አብርሃ ደስታ በኢትዮጵያዊነቱ ሰበብ ለእሥርና እንግልት ግደይ ተስፋጋብርም ለሞት ሲዳረግ ለመቀሌውና ለአዲስ አበቤው ምስኪን ዜጋ የቅብጠት ያህል ይቆጠር ነበር፡፡ ተመስገን ደሳለኝና እስክንድር ነጋ ለሕዝብ መብት በመጮሃቸው ሳቢያ ዘብጥያ ሲወርዱ ለደቻሳና ለአላምረው ደንታ የማይሰጣቸው ጊዜ ነበር፡፡ ብዙ ዕንቆቅልሾችን መዘርዘር ይቻላል፡፡ የሆኖ ሆኖ ግን ችግሩ ቀስ በቀስ የሁሉንም በር ማንኳኳቱ ተደረሰበትና ይሄውና አሁን የዐመፁ ቋያ እንደ ቋቁቻ በየክልሉ ይፈነዳዳ ጀመር፡፡ ይህ ደግሞ የምጡ መጀመሪያ እንጂ መጨረሻው ገና ነው፤ የሚጠበቀው መጨረሻ ደግሞ እግዚአብሔር ካልተጨመረበት በስተቀር እጅግ ዘግናኝ እንደሚሆን ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ከእያንዳንዱ የዳመና ጉርምርምታ በኋላ ዶፍ አለ፡፡ ምንጮችና ኩሬዎች እየሞሉ አነስተኛ ወንዞችን ያጠግባሉ፤ አነስተኛ ወንዞችም አገር አቋራጭ ትላልቅ ወንዞችን ይመግባሉ፡፡ ያኔ የሚከሰተው ጎርፍ አደገኛና በቀላሉ የማይበርድ ነው፡፡ መጠንቀቅ ያን መሰሉን ጎርፍ ነው፡፡ ልብ በሉ – እኛ ካልተጠነቀቅን ደግሞ ወያኔ ስለጎርፍ የመጨነቅ ባሕርይ የለውም፡፡ ወያኔ ማለት ራሱን እንደፍጹማዊ ፍጡር አድርጎ የሚቆጥርና ስህተት እንደማይሠራ የሚያምን የልበ ደንዳች ቡድን ነው፡፡ ይቅርታንና ምሕረትን የማያውቅ ቡድን ቢኖር ወያኔ ብቻ ነው፡፡

የአሁኑን ዘመን አያድርገውና እኛ ኢትዮጵያውያን በብልህነታችን እንታወቃለን፡፡ አሁንና ዛሬ ግን ሰው በቀደደልን የተንኮል ቦይ ገብተን በሚያስከፋ ደረጃ እየተጎዳን እንገኛለን፡፡ ሰሞኑን ደግሞ ወደ ኅሊናችን እየተመለስን የምንገኝ እንመሰላለን፡፡ ዕድሜና መከራ አስተማሪዎች ናቸው፡፡ ባሳለፍናቸው የወያኔ መሪር የአገዛዝ ዘመናት ብዙ ተምረናል፡፡ ጠላትን ከወዳጅ የሚያስለይ በቂ ግንዛቤ ጨብጠናል፡፡ የበደለን ወያኔ እንጂ የተለዬ ዘር እንደሌለ ተረድተናል፡፡ ምክንያቱም ከሞላ ጎደል ሁላችንም ተጎጂዎች ነበርንና፡፡ አንጻራዊ የጥቅም መለያየት ቢኖር ሥርዓቱ የፈጠረው ሸውራራ የአገዛዝ ዘይቤ እንጂ ከሕዝብ የመነጨ አይደለም፡፡ ስለዚህ ሕዝብና ሕዝብ መቼም ቢሆን ተለያይቶ አይለያይምና አጓቱን ከመጨለጥ ዐይቡን ማየት ያስፈልጋል፡፡ እናም መቼም ቢሆን ፍርዳችንና ተግባራችን ፍትሃዊ ይሁን፡፡

አሁን ማድረግ ያለብን ብዙ ነገር አለ፡፡ ጠላት ምን ጊዜም ጠላት ነውና መቼም አይለቀንም፡፡ እንኳንስ በነፃነት ትግል ወቅት ከነፃነት ማዶም ተሻሮ ብዙ ሊያምሰን እንደሚሞክር ግልጽ ነው፡፡ መፍትሔው ግን ቀላል ነው – እሱም መሣሪያና ትጥቅ ሣይሆን ዕውቀትንና ጥበብን መታጠቅ ነው፡፡ ከአንድ ታንክና ከብዙ ሚሣይል ይልቅ “ወንድምህን እንደራስህ ውደድ” የምትለዋ ዐረፍተ ነገር ብዙ ዋጋና ትርጉም አላት፡፡ ከአሥር የጦር አውሮፕላኖች ይልቅ “ኢትዮጵያዊ ኢትዮጵያዊነቱን፣ ነብርም ዥንጉርጉርነቱን ሊለውጥ ይቻለዋልን?” የምትለዋ ነባር መጽሐፍ ቅዱሣዊ ብሂል የበለጠ ፈውስ ናት፡፡ ከእልህና ከበቀል ስሜት ይልቅ “ወንድሜ/ጓደኛዬ ሰባት ጊዜ ቢበድለኝ ሰባት ጊዜውን ሁሉ ይቅር ልለው ነውን?” ተብሎ ለተጠየቀ ጥያቄ “ሰባት ጊዜ ሰባም ቢሆን ይቅር በለው” የተባለው የይቅር ባይነት ክርስቶሳዊ አስተምህሮ የቆረፈደን ፍቅር ያለሰልሳል፣ በጥላቻ የደነደነን ልብ ያሟሽሻል፡፡ እስካሁን የሆንነውን ሁሉ የሆንነው አንዳች የፀላዔ ሠናያት መንፈስ በመካከላችን – ወያኔን ተመስሎ – ሰርፆብን እንጂ እኛ ኢትዮጵያውያን ፍቅራችንና መተዛዘናችን እንኳንስ ለኛ ለሌላም ይተርፋል፡፡ ስለሆነም ከስሜታዊነት ፀድተንና ከቂም በቀልና ጥላቻ ራሳችንን አስወግደን ፍትሃዊ ትግል እናካሂድ፡፡ የዘሩት መብቀሉ አይቀርም፤ ተኝተው ተፉት ወደራስ መመለሱም እንዲሁ፡፡ የደም ፍላት የትም አያደርስም፡፡ አስተዋይነት ግን ብዙ ወንዞችን ያሻግራል፡፡ ከጸጸትም ይታደጋል፡፡

ስለሆነም ከሰው በኋላ የመጡ ልዩነቶቻችንን ወደጎን እንተውና ለጋራ ኅልውናችን ተባብረን እንነሳ፡፡ ከአሁን በኋላ በዘርና በጎሣ፣ በሃይማኖትና በሰው ሰራሽ ድንበር እየተቧደንን አንተላለቅ፡፡ የጠላትን ዕቅድ ከመፈጸምና ከማስፈጸም እንቆጠብ፡፡ የተጀመረው ሕዝባዊ ትግል ግቡን እንዲመታ በቀናነትና በጨዋነት በቻልነው መንገድ ሁሉ እንሳተፍ፡፡ ገንዘብ ያለው በገንዘቡ፣ ዕውቀት ያለው በዕውቀቱ፣ ጉልበት ያለው በጉልበቱ፣ … ሁሉም በየሚችለው ተባብሮ ሳይታክትና ሳይለግም ከታገለ ነፃነታችን ቅርብ ብቻ ሣትሆን እንደሚባለውም በየበራችን ሥር ናት፡፡ እነዚህ ጥቂት አሰለጦች ይህን ያህል ሊጫወቱብን የቻሉት ልዩነቶቻችንን እያራገቡ መሆኑ ተደጋግሞ የተነገረ ግልጽ እውነት ነው፡፡

ሙስሊሙ በመጀመሪያ ሰው ነው፡፡ ክርስቲያኑ በመጀመሪያ ሰው ነው፡፡ ፕሮቴስታንቱም ሆነ ብሃኢው ወይም ሌላው በሺዎች በሚቆጠሩ ሃይማኖቶች ሥር የተኮለኮለው ምዕመን ሁሉ በመጀመሪያ ሰው ነው፡፡ ዐማርኛና ትግርኛ ወይም ፈረንሣይኛና እንግሊዝኛ የሰው ናቸው እንጂ ሰዎች አይደሉም፡፡ እነዚህ ሰው ሠራሽ የሆኑ አገልጋይ ረቂቅ ትውፊቶች ናቸው – ከሸሚዝ፣ ከከናቴራና ከጫማ እምብዝም የማይለዩ፡፡ በቃ – ባሕርያዊ ያልሆኑ ከትውልድ ወደ ትውልድ በደም የማይተላለፉ የመገልገያ መሣሪያዎች ናቸው፤ በመገልገያ መሣሪያ ሰበብ ደግሞ ሰብኣዊ ፍጡር ሊተላለቅ አይገባውም፡፡ ከፈጣሪ ቀጥሎ ሰው ከምንም በላይ ነው፡፡ ቋንቋ የሚኖረው ሰው ሲኖር ነው፡፡ ሃይማኖት የሚኖረው ሰው ሲኖር ነው፡፡ ባህልና ወግ የሚኖረው ሰው ካለ ብቻ ነው፡፡ ሰው የሚኖረው ደግሞ ሀገር ሲኖር ነው፡፡ አንዳንድ ዕብዶች ብዙ ነገሮችን – የራሳቸውን ቁሣዊ ሕይወት ጭምር – ከሀገር አስበልጠው ሲመለከቱ ቢስተዋሉም እውነታው ግን ይህ ነው – ሀገር ከምንም ነገር በላይ መሆኑ፡፡ መቀመጫ ሳይኖር የት ላይ ተሁኖ ምን ነገር ማድረግ እንደሚቻል ራሳችሁ አስቡት፡፡ … መፈላሰፍ ይቅር ብዬ ነበርና ይቅርታ፡፡

ከሰው ደረጃ ደግሞ ትንሽ ዘቀቅ እንበል፡፡ ኢትዮጵያ የሰዎች መኖሪያ ናት፡፡ አላለልን ሆኖ እንጂ ወርቅ ምድር አለችን፡፡ ከእሥር ቤትነት አውጥቶ ወደ ተደላደለ የፍትህና ርትዕ ሕይወት የሚመልሰን ሰው ነው ያጣነው፡፡ ከነልዩነቶቻችን እንደሰው ተቀብሎ በእኩልና በፍትህ የሚያስተዳድረን ሰው አጣን፡፡ ልዩነቶቻችንን ለመጠፋፊያነት ሳይሆን ለጌጥነት የሚጠቀምበት በብልኆች የተሞላ መንግሥት ማግኘት ተሣነን፡፡ አንዱን ከአንዱ እየለዬ እንደጣውንት የሻጉራ ሳይመለከት በእኩል የሚሰበስበን ሰው እስካሁን በወጉ አላገኘንም፡፡ እንደ ዐወሬና እንደእንስስሳ እየቆጠረን የሚገዛና የሚነዳ ጭራቅ እንጂ እንደሰውና እንደራሱ ዜጋ ዐይቶ የሚያስተዳድር ብቁ ሰው ጠፋ፡፡ ችግራችን ይህ ነው፡፡ በተረፈ አንዱ በሌላው ላይ፣ በተለይ አንደኛው ሕዝብ በሌላ ወንድም ሕዝብ ላይ ምንም ቅራኔና ጥላቻ የለውም – ይህን እናውቃለን፡፡ ችግሩ ከላይ እንጂ ከታች አይደለምና፡፡

ነፃነታችንን የምናገኘው ከፍ ሲል የተጠቀሱትን የመሰሉ ነባር ችግሮቻችንን ስናስወግድ ነው፡፡ የአንዳችን ችግር ለሌላኛችን ሊሰማን ይገባል፡፡ ያኔ ነው አንድነት የምንፈጥረውና ኃይላችን የሚፈራው፡፡ ለተናጠል ጥቃት ከተመቻቸን ግን ሁሉም ገዢ ኃይል እየተፈራረቀ እንደእስካሁኑ መቅኖ ያሳጣናል፡፡ ሀገር አልባ ሆነን መቅረት ደግሞ የምንፈልግ አይመስለኝም፡፡

ወያኔን በሁሉም ቦታዎችና በአንድ ወቅት መወጠርና ወደ ድርድር (የማይመስል አማራጭ ነው) ወይም ወደ ሽግግር መንግሥት የሚገባበትን(የምንገባበትን) ሁኔታ ማመቻቸት ይገባል፡፡ ከዚህ ነጥብ አኳያ የትም የምትኖሩ ምሁራን ዜጎቻችን እንቅልፍ ሊወስዳችሁ አይገባም – ሲቻል በግልጽ ያ ሳይቻል ሲቀር በኅቡዕም ቢሆን በዚህ ጉዳይ ዙሪያ ብዙ መሥራት ይጠበቅባችኋል፡፡ በኋላ ሠርገኛ መጣ እንዳይሆንና የሕዝብ መስዋዕትነት በሌሎች ጭልፊቶች እንዳይሞጠለፍ ካሁኑ መጠንቀቅ ይገባል፡፡ የምንጋግረው ድፎ ሁሌም እያረረ መቸገር የለብንም፡፡

የነበሩንንና ወያኔ የዘራብንን ማኅበራዊ ቅራኔዎች በአፋጣኝ አስወግደን ወደጋራ መድረክ ካልገባን ከዚህ በባሰ እንጠፋለን፡፡ ላለመጥፋት አብነቱ ለመሠሪዎች ተንኮል አለመንበርከክና የተጣለብንን አፍዝ አደንግዝና ከፋፋይ ሤራ በጋራ ትግል ማስወገድ ብቻ ነው፡፡ የአዳምና የሔዋን ዘር ሆኖ፣ የአደምና የሃዋ ልጅ ሆኖ አንተ ትግሬ አንተ ኦሮሞ መባባል ከአለማወቅ የሚመነጭ እንጂ ከብልኅ አእምሮ የሚፈልቅ አይደለም፡፡ ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ ይባላልና እንወቅበት፡፡…

በቀደም ለት በኢሳት አንድ ዝግጅት ተከታትያለሁ – በዋሽንግተን የኢሳት ድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ ያዘጋጀው ነው፤ በዚያ ስብሰባ የሀገራችንን ሕዝብ የሚያኮራ አንድ ማለፊያ ትዝብት አለኝ፡፡ ከተናገሩት ሰዎች አንዱ ሌሊሳ የተባሉ በዋሽንግቶን የኦሮሞ ኮሚዩኒቲ ማኅበር አንድ አባል ይገኙበታል፡፡ የተናገሩት በዐማርኛ ነበር፡፡ ኢትዮጵያውን ካሏቸው የጋራ መሣሪያዎች አንዱ ዐማርኛ መሆኑ ስለሚሰማኝ በእጅጉ ተደስቻለሁ፡፡ የስሜቴ ምንጭ ዐማርኛ መነገሩ አይደለም – ያስደሰተኝ ጠላት የተበተበባቸውን ወጥመጥ በጣጥሰው ኢትዮጵያውያን ለመቀራረብ መቁረጣቸወ ነው፡፡ ባፉት ጥቂት አሠረት ዓመታት በውነቱ እኛን ዐይጥና ድመት አድርጎ በተናጠል ቀጥቅጦ ለመግዛት ያልተሸረበብን ተንኮል የለም፡፡ ከነዚህ ተንኮሎች አንደኛው አንዳችን ለአንዳችን እሬት መስለን እንድንታይና የወል ዕሤቶቻችን ላይም ጥላቻ እንዲያድርብን የተደረገው ትልቁ ዘመቻ ነው፡፡ የጠላትን መንገድ ተከትለን አላስፈላጊ ኩርፊያ በመፍጠር እየተገፈታተርን መኖራችንን ለሚረዳ ሰው ይህ ወርቃማ ጅምር ምን ዓይነት ዘላቂ መልካም ነገርን እንደሚወልድ መገመት አያቅተውም፡፡ ቋንቋ በሥነ ልቦና ልክፍት ተጠምደው የሚወዛገቡበት የማንነት መገለጫ ሣይሆን ከልደት በኋላ የሚገኝ (acquired or learned) ተራ የመግባቢያ መሣሪያ ነው ብዬ ከፍ ሲል በገደምዳሜ እንደጠቀስኩት ተፈጥሯዊ ሥነ ልሣናዊ ሂደቱን ጠብቆ ነገና ከነገ ወዲያ ኦሮምኛ ወይም ትግርኛ የኢትዮጵያ ኦፊሴላዊ ቋንቋ ሊሆኑ ይችላሉ – በዐዋጅና በሌላ ሕገ ወጥ “መንግሥታዊ” ተፅዕኖ ከሆነ አሁን እያስተዋልነው እንዳለው ዓይነት ችግር መከሰቱ አይቀርም፡፡ ቋንቋን ከጠቀሜታው አንጻር እንጂ ከቀዳሚ ተናጋሪዎቹ ማንነትና ምንነት ጋር እያስተያየን አመለካከታችንን የምንለዋውጥ ከሆነ ደግሞ የጋራ የሚባል ነገር ይጠፋና ልክ እንደባቢሎናውያን ሆነን እንቀራለን፡፡ “የኔ ያንተ ነው፤ ያንተም የኔ ነው” በሚል የአንድነት ስሜት ከተዋዋጥን ግን አንድም ችግር የለብንም፡፡ ስለሆነም ይህ ጅማሮ በጣም ድንቅ ነውና ሁላችንም ከያለንበት የግል ዓለም እየወጣንና በተቻለን መጠን ግማሽ ግማሽ መንገድ እየተጓዝን መሀል ላይ እንገናኝ፡፡ በቃ፡፡ ያኔ ችግራችን ሁሉ ታሪክ ይሆናል፡፡

Advertisements