ከኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ በጎንደር የተወሰደውን የሃይል እርምጃ በማስመልከት የተሰጠ መግለጫ


በጎንደር የተወሰደውን የሃይል እርምጃ እና የተከሰተዉን ቀዉስ በማስመልከት የተሰጠ መግለጫ
የወልቃይት ጠገዴ የአማራ ማንነት ጥያቄ አቅራቢ የኮሚቴ አባላትን አላግባብ አድኖ ለመያዝ በተደረገ ሙከራ የተነሳ ሃምሌ 4, 2008 ማለትም የኦሮሞ አብዮት በተጀመረበት ልክ በ8ኛ ወሩ በአማራ ክልል ጎንደር ከተማ ላይ ህዝባዊ ተቃውሞ ተቀስቅሷል። ይህንን ተከትሎ ከታጣቂ ሀይሎች ጋር ግጭት መፈጠሩም ተሰምቷል።

የማንነት ጥያቄም ይሁን ሌላ የመብት ጥያቄ መንግስት በህጋዊና በህገ መንግስታዊ አኳሃን ብቻ መፍታት ሲገባው እራሱም ህግና ህገ መንግስቱን አየጣሰ ሀገሪቱን ለቀውስ ዳርጓታል። በኦሮሞ አብዮትም የታየው ይሄው ነው። ለራሱም ህግን ከማያከብር ህገ ወጥ መንግስት መፍትሄ መጠበቅ አይቻልም። ስለሆነም፦

1) መብቱን በጠየቀ ህዝብ ላይ የሚወሰደውን ህገ ወጥ የሀይል እርምጃ እናወግዛለን ። በህዝብ ላይ የሚደርሰውን የሀይል እርምጃና እስራት እንዲቆም አጥብቀን እንጠይቃለን።
2) የመብት ጥያቄ በማንሳታቸውና ሀሳባቸውን በመግለጻቸው ብቻ የታሰሩ የህሊና እስረኞች በአስቸዃይ እንዲፈቱ እንጠይቃለን።
3) ባለፉት ፰ ወራት በህገ ወጥ እርምጃ የተገደሉ እና የተጎዱ ዜጎች ጉዳይ በገለልተኛ አካል እንዲጣራ እንጠይቃለን።
4) ለ 25 ዓመታት በህዝባችን ላይ የተንሰራፋዉን ፋሽስታዊ አገዛዝ አሽቀንጥረን ለመጣል በጋራ ታግለን ነጻነታችንን ከማስከበር ውጪ አማራጭ የለንም። ስለዚህ መላዉ የአገራችን ህዝብ መብቱን ለማስከበር የሚያደርገውን ህጋዊና ሰላማዊ ትግል እንዲያቀናጅ ጥሪያቸንን እናቀርባለን። በጋራ እንድቆምም እናሳስባለን።

ድል ለሰፊው ህዝብ!

የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ የአለም አቀፍ የድጋፍ ቡድን
ሐምሌ 10, 2008
ሚንያፖሊስ ፣ ሚኒሶታ

Advertisements