በጎንደር የተቀሰቀሰው አመጽ ለሁለተኛ ቀን ቀጥሏል፣ በርካታ ሰዎች ተገድለዋል፣ ከወያኔ ወገን የወደቁት አስክሬናቸው አልተነሳም


Demeke-Zewdu1የወልቃይት ሕዝብ የማንነት ጥያቄ ኮሚቴ አባላትን” ከጎንደር ከተማ አፍነው ለመውሰድ ፊታቸውን ጭምብል በመልበስ ሸፍነው ከትግራይ ክልል በመጡት የሕወሃት አፋኞችና እነርሱን በመርዳት ላይ ካሉት የፌደራል ፖሊሶች ጋር የጎንደር ሕዝብ ለሁለተኛ ቀን እየተዋጋ ይገኛል።

ወያኔዎቹን በመፋለም ላይ ያሉት አብዛኛዎቹ ወጣቶች ምንም አይነት የጦር መሳሪያ ያልታጠቁ ናቸው። ይሁንና ምንም እንኳን ከሕዝብ ወገን “የወልቃይትን ሕዝብ የማንነት ጥያቄ የኮሚቴ አባላትን” ጨምሮ ብዙ ሰዎች የወደቁ ቢሆንም በአንጻሩ ከወያኔዎቹ ጎራም በርካታ ታጣቂዎች ተገድለዋል።

የወልቃይት ሕዝብ የማንነት ጥያቄ ኮሚቴ አባላት ወልቃይት ጠገዴ በትግራይ ክልል ስር መሆን የለበትም ሕዝቡ አማራ ነው፣ መሬቱም ቢሆን በታሪክ በትግራይ ክፍለ ሀገር/ክልል ስር ሆኖ አያውቅም ስለዚህ አማሮች የመሆናችን (ማንነታችን) ተረጋግጦ በአማራ ክልል ስር መተዳደር ይገባናል የሚል ጥያቄ በማንሳታቸውና በጥያቄያቸውም እየገፉ ስለሆነ ነው የትግራይ ክልል አስተዳደር አፋኞችን ወደ ጎንደር ልኮ ጉዳዩን በኮሚቴ አባልነት የሚያንቀሳቅሱትን ግለሰቦች ለማፈን የፈለገው።

“የወልቃይት ሕዝብ የማንነት ጥያቄ ኮሚቴ አባላት” በጎንደር ሕዝብና በመላው አማራ ሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ ድጋፍ አላቸው።

ማንነታቸው የማይታወቀውና ከትግራይ እንደመጡ የሚነገረው አፋኞች ማክሰኞ ከሌሊቱ 11 ሰዓት ላይ የአፈና ተግባራቸውን ጀምረው አራት “የወልቃይት ሕዝብ የማንነት ጥያቄ ኮሚቴ አባላትን” አፍነው ወዴት እንደወሰዷቸው አይታወቅም።

አፋኞቹ የአፈና ተግባራቸውን ቀጥለው ሌላኛው የኮሚቴ አባልን (ኮ/ል ደመቀ ዘውዱ) ቤት በከበቡበት ወቅት ነበር ከአካባቢው ህዝብ ተቃውሞ የገጠማቸው “ማናችሁ፣ ማንነታችሁን የሚገልጽ መታወቂያ አሳዩን” የሚል ጥያቄ ከአካባቢው ሕዝብ የቀረበላቸው አፋኞች በሕዝቡ ላይ ተኩስ በመክፈታቸው ነገሩ ተባብሶ በርካታ ሰዎች ለመሞታቸው ምክንያት ሆኗል።

የኮ/ል ደመቀ ዘውዱም “እኔ እጄን አልሰጥም ጎንደር ተወልጄ” ብለው ከወያኔዎቹ ጋር ሲዋጉ ውለው አድረዋል።  አቶ አደራጀው ዋኘው የወልቃይት ሕዝብ የማንነት ጥያቄ ኮሚቴ ጸሃፊ ከቪኦኤ አማርኛው ክፍል ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ እንደገለጹት “እስካሁን ወያኔዎቹ ሦስት የእጅ ቦምቦችን በኮ/ል ደመቀ ቤት ላይ ጥለዋል” ብለዋል።

ኮ/ል ደመቀ ዘውዱ በሕዝቡ እርዳታ እየተታኮሱ ወጥተዋል እየተባለ ቢሆንም ዜናውን ያሰራጨው ኢሳት (የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን) ኮ/ል ደመቀ ያሉበትን ሁኔታ ለማረጋገጥ አለመቻሉን ገልጿል።

ይህን ዜና እያጠናቀርን ባለንበት ወቅት በጎንደር ከተማ በከባድ መሳሪያ የታጀበ ከፍተኛ ተኩስ እየተደመጠ መሆኑን ወደ ጎንደር ስልክ የደወሉ በርካታ ሰዎች አረጋግጠዋል።

ወጣቶቹ ቀደም ሲል የሕወሃት (ወያኔ) ንብረት የሆነውን “ሰላም ባስ” እና አንድ ሌላ ተሽከርካሪ ከማቃጠላቸው በተጨማሪ የሕወሃት ሰላዮች ናቸው ተብለው የሚታመኑ ንብረቶችንም ሳያወድሙ እንዳልቀሩ ይነገራል።

በጎንደር የተለያዩ ወረዳዎች እና ዞኖች ሕዝብ የጎንደር ከተማን ሕዝብ ለማገዝ መንቀሳቀሱን ምንጮች ይጠቁማሉ።

Advertisements