አቶ አንዳርጋቸው ፍርድቤት የማይቀርቡ ከሆነ እስረኞችን በነጻ እፈታለሁ ሲል ፍርድ ቤቱ ማስጠንቀቂያ ላከ


573C78Cኢሳት ዜና :- በዘመነ ካሴ መዝገብ በሽብር ወንጀል ተከሰው ከአመት በላይ በእስር ቤት በስቃይ ላይ የሚገኙት አቶ አሸናፊ አካሉ ፣ ደህናሁን ቤዛ፣ ምንዳየ ጥላሁንና አንሙት የኔዋስ፣ በመከላከያ ምስክርነት የጠሩዋቸው አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ እንደቀርቡላቸው በተደጋጋሚ ቢጠይቅም፣ ቃሊቲ እስር ቤት ለማቅረብ ፈቃደኛ አለመሆኑን ተከትሎ ከፍተኛው ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት ለእስር ቤቱ ሃላፊዎች “ ለምን ሰው ይንገላታል፣ ሰበር ሰሚ ችሎት ሳይቀር እንዲቀርብ የወሰነው ለምን አይቀርብም፣ እናንተ አላቀርብም በማለታችሁ ተከሳሾች አንድ አመት በእናንተ የተነሳ እየተንገላቱ ነው” በማለት ከተናገረ በሁዋላ፣ አቶ አንዳርጋቸው ሃምሌ 7 ቀን 2008 ዓም ፍርድ ቤት የማይቀርቡ ከሆነ ተከሳሾችን በነጻ እናሰናብታለን ሲል ሰኔ 30 ቀን 2008 ዓ.ም. በዋለው ችሎት ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።

ተከሳሾቹ ከአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ጋር ኤርትራ ውስጥ በመገናኘት የተለያዩ ትዕዛዞችን ተቀብለዋል የሚል ክስ የቀረበባቸው ሲሆን፣ እነሱም ከአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ምንም አይነት ትእዛዝ አለመቀበላችንን ለማረጋገጥ አቶ አንዳርጋቸው ቀርበው ይመስክሩልን ሲሉ መከራከሪያቸውን አቅርበዋል። ዓቃቤ ሕግ አቶ አንዳርጋቸው ፍርድ ቤት እንዳይቀርቡ በሰበር ሰሚ ችሎት አሳግዶ ቢቆይም ፣ ሰበር ሰሚ ችሎቱ የአቃቢ ህግን ይግባኝ እንደማይቀበለው በመግልጽ አቶ አንዳርጋቸው ቀርበው እንዲመሰክሩ ብሎአል።

የአስር ቤት አስተዳደር አቶ አንዳርጋቸው ቃልቲ እስር ቤት እንደሌሉ በተደጋጋሚ ሲገልጽ ቆይቷል። ይሁን እንጅ የእንግሊዝ አምባሳደርም ሆኑ የአቶ አንዳርጋቸው አባት፣ አቶ አንዳርጋቸውን ቃልቲ ድረስ በመሄድ ጠይቀዋቸዋል።

አቶ አንዳርጋቸው ከ4 ቀናት በሁዋላ ፍርድ ቤት የሚቀርቡ ከሆነ፣ ከየመን ታፍነው ከተወሰዱ ከ3 አመታት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ በህዝብ ፊት በአካል ይቀርባሉ ማለት ነው። አቶ አንዳርጋቸው በህዝብ ዘንድ ያላቸው ተቀባይነት ከፍተኛ መሆን በህዝብ እንኳን እንዳይጎበኙ ተደርጓል።

Advertisements