ወያኔዎች የሚደነባበሩት ቁልፉ ከአቶ መለስ ጋር ተቀብሮ ነው፡፡ – ይገረም አለሙ


አስቀድሞ የታወቀ ከሞታቸው በኋላ ደግሞ በራሳቸው ሰዎች የተረጋገጠ ነገር thቢኖር አቶ መለስ ህውኃትም ፣ኢህአዴግም፣መንግሥትም በጥቅሉ ሁሉም ነገር አንደነበሩ ነው፡፡ይህን ሀሰት በማለት አይኔን ግንባር ያድረገው ጆሮየንም ቀንድ የሚል ካለ መለስ ብሎ እነ አቶ በረከት የተነገረውንና የተጻፈውን ይመልከት፡፡

አቶ መለስ በሞት አፋፍ ላይ በነበሩበት ግዜ አንደሚሞቱ አምነው መቀበል ተስኖአቸው ይሁን ወይንም ቁልፉን የሚያስረክቡት ሰው ባለማግኘት ወይንም ቁልፉ ሊያስነሳ የሚችለውን አደጋ በማወቃቸው አለያም በሥልጣን ዘመናቸው ከርሳቸው በስተቀር ሌሎች አንዳያውቁት ቆልፈውት የኖሩትን ሁሉ አንደቆለፉት ለመሄድ በመፈለግ ባይታወቀቅም ቁልፉን ሳያስረክቡ ነው የሞቱት፡፡ ይህንንም በወያኔ ሰፈር የታየውና እስከ ዛሬም የቀጠለው መደነባበር ይመስክራል፡፡

ባላሥልጣናቱም ቢሆኑ የአቶ መለስ ወደ ሞት እየሄዱ መሆን በተረጋገጠበት ወቅት ቁልፉን ለመረከብ አልደፈሩም ወይንም አልፈለጉም፡፡ አንደውም በወቅቱ የእነርሱ ስራ የነበረው ሞት በፕሮፓጋንዳ ይመለስ ተደብቆም ይቀር ይመስል በጠና መታመማቸውን ማስተባበል ኋላም መሞታቸውን መደበቅ ነበር፡፡

በርግጥ ቁልፉን ከመረከብ ይለቅ ከአቶ መለስ ጋር መቀበሩን ሊመርጡ የቻሉበትን ምክንያት መገመት ይቻላል፡፡ ርክክብ ይከናወን ቢባል በወቅቱ ምክትል ጠቅላይ ምኒስትር የነበሩት አቶ ኃይለማሪያም እጅ ነው ሊገባ የሚችለው፡፡ ይሄ ደግሞ በህውኃቶችም ሆነ እንደእቅምቲ በብአዴኖችና ኦህዴዶች አይፈለግም፡፡ ስለዚህ የመሪያቸው መመሪያ የሆነውን ከበጣም መጥፎ መጥፎውን መምረጥ ግድ ሆነና የምስጢሩ ቁልፍ ከአቶ መለስ ጋር አንዲቀበር ምርጫቸው ሆነ፡፡ ለዚህ ደግሞ በአቶ መለስ ሞት ማግስት ምክትል ጠቅላይ ምኒስትርነት ለየድርጅቶቹ አንዲዳረስ መደረጉ አንድ ማሳያ ነው፡፡ ሹመቱን ተካፈሉት ቁልፉን ግን ሊካፈሉት አይችሉም፡፡ቁልፉ (ፓስ ወርዱ) ሁሉም እጅ ቢገባ ደግሞ ምን ሊሆን እንደሚችል አይታወቅም፡፡ ስለሆነም ለመገመት የማይቻል አደጋን ከመጋፈጥ ውጤቱ የሚታወቀውን አደጋ መቀበል ምርጫቸው ሆነና ቁልፉ ከአቶ መለስ ጋር አብሮ ተቀበረ፡፡

ራሳቸው እነደነገሩን በሀገሪቱ የተካሄዱና በመካሄድ ላይ ያሉ ነገሮች ሁሉ ሀሳቡ፣ እቅዱ፣ የአፈጻጸም ስትራቴጂው ወዘተ የአቶ መለስ ነው፡፡ አነርሱ የሚነገራቸውን እየተቀበሉ የሚታዘዙትን እየፈጸሙ የኖሩ በመሆናቸው ቁልፉን ሲያጡ የመጀመሪያ ተግባራቸው መሆን የነበረበት ሁሉንም ነገር ሊያውቁት፣ ሊፈጽሙና ሊያስፈጽሙት በሚያስችላቸው መልኩ መሰረታዊም ባይሆን መለስተኛ ለውጥ በማድረግ ማመቻቸት ነበር፡፡

ነገር ግን በአቶ መለስ ተጠርንፎ ተይዞ የነበረው የሥልጣን ፍላጎታቸውና አለመተማመናቸው ለዚህ የሚያበቃቸው ሳይሆን ቀረና የእኛ የሆነ ምንም ነገር የለም የአቶ መለስን ሌጋሲ ነው የምናስፈጽመው በማለት መነሻውን፣መሄጃ አቅጣጫውንና መድረሻ ግቡን የማያውቁት ባቡር ላይ ተሳፍረው መደነባበሩን ተያያዙት፡፡ ወያኔዎች የምስጢሩ ቁልፍ ከአቶ መለስ ጋር በመቀበሩ ምክንያት እየተደነባበሩ ስለመሆናቸው ዘመነ መለስንና ዘመነ ኃይለማሪያምን ማነጻጸር ነው፡፡

በአቶ መለስ ግዜ አይደለም ዜና ስድብና ዘለፋ ሳይዛነፉ ነበር ከቤተ መንግሥት እስከ ቀበሌ ጽ/ቤት የሚደርሱት፤ አቶ መለስ አንኳን ይቅርታ ጠይቀው( አድርገውት አያውቁም እንጂ) ስድባቸው አንደመመሪያ የሚከበር አንደ መፈክር የሚሰተጋባ አንደነበር አይዘነጋም፡፡ ህውኃት ከእንጥሏና ከጭንቅላቷ በስብሳለች ባሉበት ግዜ ከመቀሌ እስከ ሶማሌ፣ ከሀረር እስከ ጎንደር የሚገኝ ካድሬም ጋዜጠኛም እነዴት እየተቀባበለ አንዳስተጋባው እናስታውሳለን፡፡ ዛሬ ግን የጠቅላይ ምኒስትሩን ይቅርታ ከቁብ ያለመቁጠር፣ በአንድ ጉዳይ ከየባለሥልጣናቱ የተለያየ ነገር መስማት፣ ከቃልም አልፎ የራስ ያልሆነን ፎቶ እየለጠፉ መቀላመድ ሲነቃም ይቅርታ መጠየቅ የተለመደ ሆኗል፡፡ ( በማህበራዊ ድረ ገጽ የወጣው ተማረከ የተባለው መሳሪያ፣ ተሰራ የተባለው የውስጥ ለውስጥ የባቡር መስመር ወዘተ ይጠቀሳልሉ)

የደምቢ ዶሎው አውሮፕላን ማረፊያ የተሰራበት ተብሎ በዜና ማሰራጫ የተነገረውና ሶስት የተለያየና እጅግ የተራራቀ የገንዘብ መጠን የተገለጸባቸው ሰሞነኛ ዜናዎች ደግሞ እነርሱ ሀፍረት ባይፈጥርባቸም ለእኛ ለዜጎች የሚያሳፍርና ሰዎቹ ሕዝቡን ረግጠው በመግዛቱ ብቻ ሳይሆን የሀገሪቱን ሀብት በመዝረፉም ስምምነት እንደሌላቸው የሚያሳይ ነው፡፡ መቼም አንዲህ አይነት ዜና በአቶ መለስ ግዜ ደፍሮ የሚሰራም የሚያሰራም አይታሰብም፡፡ የኮንዶሚኒየም መጥፋትና በስኳር ኮርፖሬሽን ስም የተበላው ገንዘብ ለፓርላማ ሊቀርብ ለሕዝብም ጆሮ ሊደርስ መቻሉም የመደነባበራቸውና የእርስ በርስ ሽኩቻቸው ውጠየት ነው፡፡

በዶ/ር አዲሱ ገብረእግዚአብሄር የሚመራው የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ተብየ ተቋም ለፓርላማው ሪፖርት ያቀረበበት ሁኔታም ጤነኛነታቸውን አያሳም፡፡ አንደተከታተልነው ከሆነ ዶ/ሩ ሁለት ገጽ የሚሆን ማስታወሻ አዘጋጅተው ለፓርላማው ታደለ፡፡ እርሳቸውም ይህንኑ አንብበው በኦሮምያ የተፈጸመው ግድያ ህጋዊ፣ የተወሰደውም ርምጃው ተመጣጣኝ ነው፣በአማራ ቅማንት ለተፈጸመው የአማራ ክልል ይቅርታ ይጠይቅ ካሳ ይክፈል አሉ፡፡ በዚህ ሪፖርት ሳይሆን ገለጻ ያልተደሰቱ ደግሞ የተሰጣችሁን ወረቀት ይዛችሁ እንዳትወጡ እባካችሁ ይህ ነገር ከጋዜጠኞች እንዳይደርስ በማለት የፓርላማ አባላቱን ተማጸኑ፡፡ በአፍቅሮተ ወያኔ የታወረ ሰው እንኳን ቢሆን ይህ የመደነባበር ማሳያ አይሆንም ሊል የሚችል አይመስለኝም፡፡

የኦሮምያ ክልል ሕዝባዊ ተቃውሞን በተመለከተም የተወሰደው ርምጃም ሆነ ሲሰጥ የነበረው መግለጫ የተማከለ ሳይሆን በአድራጊዎቹና ተናጋሪዎቹ ስሜትና ፍላጎት የሚካሄድ ነበር የሚመስለው፡፡አቶ ጌታቸው ሕዝቡን ሰይጣን አጋንንት ድርጊቱን የጸረ ሰላም ኃይሎች ወዘተ ሲሉ አቶ አቡዱላ የሕዝቡ ጥያቄ ትክክል ነው ያልተገባ ስም አየሰጡ ማውገዝ ተገቢ አይደለም አሉ፡፡ የክልሉ ፕሬዝዳንት ደግሞ በሕዝብ ላይ የተፈጸመው ግድያ ተገቢ መሆኑን ከመግለጽ አልፈው ገዳዮቹን ለፈጸሙት ተግባር በኦሮምያ መንግሥት ሥም አመሰገኑ፡፡ ይህን ሁሉ እየሰማንና እየታዘብን አጃኢብ ሰንል ጠቅላይ ምኒስትሩ ብቅ አሉና በማንም ላይ ጣታችንን አንቀስርም የተቃውሞው መነሻ ምክንያት የእኛው ችግባር ነው ለሆነው ነገር ይቅርታ አንጠይቃለን አሉ፤፡ በዚህ የጠቅላይ ምኒስትሩ ይቅርታ መጠየቅ የሆነውን ሁሉ ለመርሳት የዳዳቸውና ወያኔ በአንድ ጀንበር የተለወጠ አድርገው ለማሰብ የከጀላቸው ሰዎች እንደነበሩ አሌ የሚባል አይደለም፡፡

ነገር ግን ያለንበት ወቅት መሪው የማይታወቅበት፣ ሁሉም ሥልጣኑንና ጉልበቱን ለማሳየት የሚንጠራራበት መንግስት አልባ የድንብርብር ግዜ በመሆኑ ሌላኛው መንግሥት ጠቅላይ ምኒስትሩ የእኛ ጥፋት ነው ያሉትን ጆሮ ዳባ ብሎ ሥልጣኑንም ጉልበቱንም ለማሳየት እነ አቶ በቀለ ገርባን ለህዝባዊ ተቃውሞው መነሳት ምክንያት አድርጎ በአሸባሪነት ከሰሰ፡፡ በጠቅላይ ምኒስትሩ ደረጃ የችግሩ ምክንያት እኛው ነን በማንም ላይ ጣት አንቀስርም በተባለበት ጉዳይ ማንም ተጠያቂ ሊሆን ባልተገባ ካልሆነም ደግሞ የጠቅላይ ምኒስትሩ ምስክርነትም ሆነ ይቅርታ መጠየቅ ባላስፈለገ ነበር፡፡

በጠቅላይ ምኒስትሩ ቢሮ የተደረገ ጥናት የተባለ ሰነድ ለውይይት የቀረበበት ስብሰባ በኢቲቭ ሳይቀር ተላልፎ የብዙዎችን ከተቃውሞው ሰፈር የሚገኙትን ሳይቀር ልብ ለማማለል ችሎ አንደነበረም እናስታውሳለን፡፡ ነገር ስራው ሁሉ የየራስን አቅም ለማሳየት የሚከናወን ማእከላዊነት የሌለው አለቃና ምንዝሩ የማይታወቅበት የድንብርብር ሆነና በጥናቱ የተገለጹ ችግሮች ሊታረሙ፣ አጥፊዎቹ ለህግ ሊቀርቡ ቀርቶ ውሾን ያነሳ ውሾ ይሁን ተብሎ ጥናት ተብዬው የውኃ ሽታ ሆኖ ቀረ፡፡

አንዱ የተናገረውን ሌላው ማፍረስ፣ጠዋት የሰሩትን ማታ ማስተባበል በአንድ ጉዳይ ላይ የማይገናኝ አሀዝ እየጠቀሱ ዜና መስራት፣ማሰራት፤ ይቅርታ እየጠየቁ መግደል ማሰርና መክሰስ ወዘተ የምስጢሩን ቁልፍ ካለማግኘትና ሀይ ባይ አንድ ኮርማ ካለመኖሩ የተከሰተ የፉክክርና የመደነባበር ውጤት ነው፡፡ በዚህ ደግሞ ተጎጂው ሀገርና ሕዝብ ነው፡፡ ግን እስከ መቼ አንደዚህ ?

ይህችን ጽሁፍ ለመላክ ስዘጋጅ በአሜሪካ ድምጽ የአማርኛው አገልግሎት የተሰማው ዜና ከላይ የጠቃቀስኩትን የወያኔዎች መደነባበር የሚያሳይና ሀገሪቱ በማንና በምን ሁኔታ ነው እየተመራችያለችው የሚለውን ጥያቄ የሚያጠናክር ነው፡፡ ነገሩ አንዲህ ነው፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ ሰኔ 19/2008 ም በባህር ዳር ከተማ ሕዝባዊ ስብሰባ ለማካሄድ አስቦ ለሚመለከተው ክፍል የሳውቃል፡፡ መስተዳድሩ ባላችሁት ቀን ስለማይቻል ቀን ቀይሩ በማለት በደብዳቤ በማሳወቁ ፓርቲው ስብሰባውን ወደ ሰኔ 26/2008 ያዛውርና የመስተዳድሩን ይሁንታ አግኝቶ ቅስቀሳ ሲጀምር ለቅስቀሳ የተሰማሩት አባላቱ በሙሉ በጸጥታ ኃይሎች ታሰሩ፡፡ ማነው የበላይ መስተዳድሩ ወይንስ ባለጠመንጃው ? ይክልሉ ፖሊስና ደህንነት በክልሉ መስተዳድር አይታዘዝም ማለት ነው? ከሆነስ ትዕዛዝ የሚቀበለው ከማን ነው? በአቶ ጌታቸው ከሚመራውና ራሱን አንድ መንግሥት ካደረገው የደህንነት ተቋም ይሆን?

ይህ የወያኔዎች መደናበርና መሻኮት የሚጎዳው እነርሱኑ ብቻ ቢሆን ባልከፋ ነበር፣ግን አለመሆኑን በተግባር እያየነው ነው፤ በሁለት ዝሆኖች መራገጥ የሚጎዳው ሳሩ ነው አይደል የሚባለው፡፡ ቢያንስ ከነ ደደቢት ህልማቸውና ጸረ ኢትዮጵያ አቋማቸው አዛዥና ታዛዡ ተለይቶ አንድ ማእከላዊ አመራር መኖር ካልቻለ ከመጥፋታቸው በፊት ያጠፉናልና መደነባበራቸውንም ሆነ መሻኮታቸውን የራሳቸው ጉዳይ ብለን የምናልፈው ሊሆን አይገባም፡፡

Advertisements