አታሸንፏቸውም ! ምክንያቱም እነሱ ናቸውና! (ሄኖክ የሺጥላ)


Woyane-788-0 (1)ማንነት በመልካምድር እና በአየር ጠባይ የሚቀየር ነገር አይደለም ። ወያኔ ትግሬን ስቃወም የተቃወምኩት አማራ ስለሆንኩ አይደለም ይልቁንም ሰው ስልሆንኩ እንጂ !

ህውሓት ጠላት ነው ያልኩት አማሪካ ስለምኖር አይደርስብኝም ብዬ አስልቼ አይደለም ። ኢትዮጵያም እቃወም ነበር ። የነሱ ምርጥ ካድሬዎች ህውሃት ብሆን እንዴት የሚመች ኑሮ ልኖር እንደምችል የነገሩኝ ምቾት በሚያጓጓበት ሃገር እና እድሜ ላይ ሆኘ ነው ። ግን አላደረኩትም! ምክንያቱም ጥያቄ ምቾት የማጣት ሳይሆን ፍትህ የማጣት ፥ መብት የመነጠቅ ስለነበረ ። ማሳያው ባንፃሩም ቢሆን ምቾት ባለበት ሃገር እየኖርኩም ከነሱ ጋ ያለኝን ፀብ አላቆምኩም ! ወደፊትም አላቆምም! መብቴ እስኪከበር ድረስ!

በተራ ሴራ ፥ ክስ ፥ ተንኮል ፥ ስም ማጥፋት እና መሰል ነገሮች የምትቀብሩት ስብዕናም ሆነ ፥ የምታለሳልሱት ማንነት እኔ ውስጥ የለም ። ተራራ እያነደዳችሁ ፥ ድልድይ እያፈረሳችሁ ፥ ጦር እየደረመሳችሁ ከተማ ስለመድረሳችሁ ከልጅኔቴ ጀምሬ በናተው ተግቼ ነው ያደግሁት ። እናንተ እንዳሰባችሁት ግን ያቃጠላችሁት ታንክ ፥ በክራንች ቆሞ እንዲለምን ያደረጋችሁት ወታደር ፥ የገደላችሁት ወጣት እንደ አንድ ሃያል ፥ የማይደፈር እና የማይነካ አካል እንዳያችሁ ሳይሆን ፥ ይህ ሁሉ ድርጊታችሁ ከአቅመቢስነት እና ከፍርሃት የመጣ እንደሆነ ነው የተረዳሁት። አለበለዚያ የ ስድስት አመት ልጅ ገሎ « ባንክ ሊዘርፍ ሲል ነው የገደልነው » የሚል ስርአት እንዴት እና ስለምን ያስፈራኛል ? ያናድደኛል እንጂ! ያስቆጣኛል እንጂ !ጥርሴን ያስነክሰኛል እንጂ! ስለምን የገበሬ መሬት ቀምቶ ፎቅ የሰራን አካል እፈራለሁ ? ስለምን ምርጫ ገልብጦ « ንጉስ ነኝ» የሚልን ግዑዝ እሸሻለሁ ? እጋፈጣለሁ እንጂ ! እታገላለሁ እንጂ ! ህዝቡን የወንጀላችሁን ልክ አሳውቃለሁ እንጂ ! አልፈራም!

የተሸነፈ ሰው አሸናፊ የሚሆነው ፥ አሸናፊው ማሸነፉን ካላወቀ ብቻ ነው ! ከካደ ብቻ ነው ! ማሸነፉን ካሸነፈው በተሸናፊነት ልቦና አሳልፎ ከሰጠ ብቻ ነው ። እኔ እየታገልኩ ብሞት እንኳ በናንተ አልሸነፍም ፥ ምክንያቱም ከሞቴ ብቀሰቀስ ድጋሚ እታገላችኋለሁና! አልቆምም ! አላቆምም! እመኑኝ እታሸንፉኝም! ስለ ምንም ምክንያት ሲባል ለናንተ የሚጎነበስ ራስም ሆነ የሚንበረከክ ጉልበት የለኝም ! ለምን ቢሉ እኔ ነኝና! ለምን ቢሉ ኢትዮጵያም እኔ አማሪካንም እኔ !

ይህ የኔ ብቻ ሳይሆን የብዙ የቁርጥ ቀን የኢትዮጵያ ልጆች መንፈስ ነው ! አታሸንፏቸውም ! ምክንያቱም እነሱ ናቸውና!

Advertisements