ዓይነ ሥውሩ የኤሌክትሪክ ሰራተኛ አበበ ነጋሽን እናስተዋውቃችሁ…


ሸገር ልዩ ወሬ፣
ዓይነ ሥውሩ የኤሌክትሪክ ሰራተኛ አበበ ነጋሽን እናስተዋውቃችሁ…
ገና በልጅነቱ በኩፍኝ ሳቢያ የዓይን ብርሃኑን ያጣው አበበ ትውልዱ ዋግ እምራ መሆኑን ይናገራል፡፡
የዕለት ጉርሱን ፍለጋ አዲስ አበባ የመጣው አበበ ውሎውን መርካቶ፣ ማደሪያውን በ“ኬሻ በጠረባ” ቤቶች አደረገ፡፡
“ኬሻ በጠረባ” – እጅግ ርካሽ የሆኑ የጋራ ማደሪያ ቤቶች ናቸው፡፡
አንድ ቀን ታዲያ በሚያድርበት የኬሻ በጠረባ ቤቶች ጣሪያ ላይ ያሉ ድመቶች ሲጣሉ የአሌክትሪክ ገመዱን በጣጥሰውት ቤቱን ጭለማ ዋጠው፡፡
ይሄኔ ዓይናማዎቹ “እንደው ምን ይሻላል…” እያሉ ባሉበት፤ ዓይነ ሥውሩ አበበ “አይዟችሁ ችግር አይግባችሁ እኔ እሰራዋለሁ” ብሎ የተበጣጠሰውን የአሌክትሪክ ገመድ ቀጣጥሎ ቤቱን ብርሃን ሞላው፡፡
ሁሉም ጉድ አለ፡፡
ከዚህ በኋላ እንግዲህ አንዱ ለሌላው እየተናገረ፣ አምኖ የሚያሰራው ሲያገኝ፣ ከስንት አንዴም ቢሆን ከአምፖል መቀጠል እስከ የኤሌክትሪክ ምጣዶችና ምድጃዎችን መስራቱን ተያያዘው፡፡
በዚህም ኑሮውን ይደጉም ገባ፡፡
የሸገር ልዩ ወሬ አዘጋጁ ወንድሙ ኃይሉም የአበበን ችሎታ ፈትኖ ማረጋገጡን ይነግረናል፡፡
አበበ ኤሌክትሪክ ለመስራት ቆጣሪውን ካጠፋ በኋላ ለጥንቃቄ በትክክልም ኤሌክትሪክ መጥፋቱን ለማረጋገጥ ሞባይሉን ቻርጀር ላይ ይሰካዋል፡፡ ይሄኔ ሞባይሉ ላይ ያለው አፕልኬሽን ቻርድ እያደረገ መሆን አለመሆኑን በድምፅ ይነግረዋል፤ በዚህም አሌክትሪክ መጥፋት አለመጥፋቱን ያውቃል ማለት ነው፡፡
ከዚያም ጥገናውን ይጀምራል፡፡
ሰርቶ ከጨረሰም በኋላ በዚሁ መንገድ አልያም የአምፖል ብርሃን ፊቱ ላይ ሲበራ ግንባሩ ላይ በሚታየው ፈካ የሚል የብርሃን ስሜት በመመራት አምፖሉ መብራት አለመብራቱን እንደሚያውቅ ይናገራል፡፡
ይህን ሁለተኛውን ዘዴ ዓይናማዎቹም ዓይናችሁን ጨፍናችሁ አምፖል መብራት አለመብራቱን ማረጋገጥ ትችላላችሁ ይለናል አበበ፡፡
ሽሮሜዳ አካባቢ ባለው ድል በትግል ትምህርት ቤት የ8 ክፍል ተማሪ የሆነው ዓይነ ስውሩ ኤሌክትሪሺያን አበበ ነጋሽ ኤሌክትሪክ የጠፋባቸው ቤቶች እየተመራ ሄዶ ለዓይማዎች ላምባዲና እየሆነ ነው ይለናል ይህ የወንድሙ መሰናዶ…
ሙሉውን ፕሮግራም ያዳምጡ (SHEGER FM 102 1 RADIO)

Advertisements