በምዕራብ አርሲ ሰልፈኞች እስርቤት ሰብረው ከ100 በላይ የፖለቲካ እስረኞችን አስለቀቁ | 3 ቤተክርስቲያኖች ወድመዋል


arsi-today-westበምዕራብ አርሲ ሻላ ወረዳ ማዕከል በሆነችው አጄ ከተማ ዛሬ ሙሉ ቀን ከተማዋ ሳትረጋጋ መዋሏን ዘ-ሐበሻ ስትዘግብ ውላለች:: የሟች ወታደሮች ቁጥር ከ8 እንደሚበልጥ በተነገረበት በዚህ ወቅት በፖሊስ የተገደሉ ሰላማዊ ሰልፈኞች ቁጥርም 4 እንደደረሰ የዘ-ሐበሻ የዜና ምንጮች አስታውቀዋል::
የኦሮሚያ ሚድያ ኔትወርክ በሰበር ዜናው እንዳስታወቀው በምዕራብ አርሲ ሻላ ወረዳ የሚገኘውን እስር ቤት ሰልፈኞች ሰብረው በመግባት በእስር ቤቱ ውስጥ ታጉረው የነበሩ ከ100 በላይ እስረኞችን አስለቅቀዋል::
አካባቢውን የወረሩት የፌደራል ፖሊሶች ሕዝቡን መግደል ከጀመሩ በኋላ ሕዝቡም እርምጃ ተመሳሳይ እርምጃ መውሰዱን ዘ-ሐበሻ ቀደም ብላ መዘገቧ አይዘነጋም::
ይህን ከባድ ተቃውሞ ለማብረድ ፖሊስ ወደ ሕዝብ በመተኮሱ ምክንያት ተቃውሞው ተብብሶ ወደሌሎች ቀበሌዎች ተዛምቷል:: በአካባቢው በአካባቢው የሚገኙ 3 ቤተክርስቲያኖች ወድመዋል: በምእራብ አርሲ የወደሙት ቤተክርስቲያኖች የሎቄ ቅዱስ አማኑኤል ቤ/ክ; የብሊቶ ቅዱስ ገብርኤል ቤ/ክ እና የአለም ጤና ቅዱስ ሚካኤል ቤ/ክ ናቸው::: እንደ አይን እማኞች ገለጻ በተቃውሞው የተደናገጡት የመንግስት ካድሬዎች የሕዝቡን ተቃውሞ ከሃይማኖት ጋር ለማያያዝ እና ለመከፋፈል ካድሬዎቹ እነዚህን አብያተ ቤተክርስቲያናት አውድመውታል::
arsi today
በ2007 በተደረገ የሕዝብ እና ቤት ቆጠራ በምዕራብ አርሲ 80% የሚሆኑ ሰዎች የ እስልምና እምነት ተከታይ ሲሆኑ 11.04% የኦርቶዶክስ እንዲሁም 7.02% የሚሆኑ የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች ተከባብረው ይኖሩበታል:: አንድ የፖለቲካ ተንታኝ ለዘ-ሐበሻ ሲገልጹ “በዚህ አካባቢ ሙስሊሙና ክርስቲያኑ ተከባብሮና ተፋቅሮ የኖረበት ነው:: ሆኖም ግን አሁን ጉዳዩን ከሃይማኖት ጋር ለማገናኘትና የኦሮሞ ሕዝብን ትግል ክርስትናን ከማጥፋት ጋር በማያያዝ መንግስት ሊከፋፍለው እየሞከረ ነው:: ዛሬ ቤተክርስቲያን ያወደሙትም ለዚሁ ነው” ይላሉ:: እንደ እኚህ የፖለቲካ ተንታኝ ገለጻ “መንግስት ሁልጊዜ ሲጨንቀው በሃይማኖት ተቋማት ላይ ጥፋት በማድረስ ሕዝብን ለማናከስና እንዳይተማመኑ ለማድረግ መሞከሩ የተለመደ በመሆኑ እንዲህ ያለውን አደጋ በንቃት ሊመለከተው ይገባል::”
በምዕራብ አርሲ በሻሸመኔ ከተማን ጨምሮ ሌሎች ወረዳዎችና ቀበሌዎችም እንዲሁ ተቃውሞው በሰፊው ቀጥሎ ውሏል::

Advertisements