የሕዝቡ ጥያቄ ትክክል ነው — የተሰጠው ምላሽስ? (ይገረም አለሙ)


የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን የሚባለው ሰበብ የአቶ አባይ ጸሀዬ ልክ እናስገባቸዋለን ዛቻና ፉከራ አቀጣጣይ ሆኖ የተቀሰቀሰው የአመታት ብሶት የወለደው ቁጣ የህዝብን ሀያልነት እያሳየ ነው፡፡ ወያኔ ጥያቄዎችንና ተቃውሞን ሲያፍንና ሲጨፈልቅ በኖረበት ስልት ይህንንም ለማዳፈን ያደረገው ጥረት ሁሉ አልተሳካለትም፡፡ የጠባቦችና የትምክህተኞች ጥያቄ ነው ኦነግና ግንቦት 7 ከበስተጀርባ አሉበት በማለት መልኩን ለማስለወጥ ሞከረ፤ አልሆን ሲለው አረመኔ ገዳይ ቡድን አሰማርቶ ገደለ ደበደበ አሰረ አልተቻለም፤ ገዳዮችን በማመስገን ለተጨማሪ ግድያ አበረታታ ህዝቡንም የማያዳግም ርምጃ አንወሰዳለን በማለት አስፈራራ፡፡ ህዝቡ ግን ወይ ፍንክች እንዳለ ነው፡፡ የሚችለውን ሁሉ አድርጎ ሲያቅተው የኦሮምያ ጉዳይ የኦህዴድ ነው አለ፡፡

ከዚህ ሁሉ በኋላ ነው እንግዲህ ኦህዴድ ማስተር ፕላኑ ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል መልኩ ህዝቡ በነቂስ ስለተቃወመው ተግባራዊ አይሆንም የሚል መግለጫ እንዲያወጣ የተደረገው፡፡ መግለጫው ሌሎች ሁለት ነገሮችንም ይዟል:: በህገ መንግሥቱ ተጽፎ የሚገኘውንና ሌሎች በመጠየቃቸው ለእስርና ለእንግልት የተዳረጉበትን የኦሮምያ ክልል ከአዲስ አበባ ያገኛል የተባለውን ልዩ ጥቅም ተግባራዊ እንደሚያደርጉ፣ የኦሮምያ ክልል በቅርቡ ያወጣው ከተሞችን የሚመለከተውን አዋጅም እንደሚያሻሽሉ ገልጸዋል፡፡

መግለጫው አንድም የዘገየ ነው፡፡ ሁለትም በኦህዴድ ሥልጣን ሊወጣ የማይገባው የመንግስትና የፓርቲን ሥልጣን ያልለየ ነው፡፡ ሶስተኛም እወነቱን ደፍሮ ያልተጋፈጠ በትእዛዝ የወጣ የሚመስል ነው፡፡

ፕሮግራሙና መተዳደሪያ ደንቡ በህውኋት ተዘጋጅቶ መሪዎቹም በወያኔ ተሾመውለት የተመሰረተውና ሀያ አራት አመት ሙሉ በወያኔ ቀጥተኛ ትዕዛዝ የሚንቀሳቀሰው ኦህዴድ ራሱን ካልለወጠ በስተቀር ከዚህ ውጪ ማድረግ አይችልም፡፡ ኦህዴድ ውስጥ ራስን ለመሆን የሚሹ መንፈራገጦች እንዳሉ የሚያሳዩ አንዳንድ ነገሮች ቢኖሩም በየግዜው ጠባብ አመለካከት ያላቸው ቢፋቁ ኦነግ የሚሆኑ ወዘተ እየተባሉ እየተመቱና እየተስፈራሩ ጎልተው ሊወጡ ባለመቻላቸው ኦህዴድ ዛሬም በሎሌነት የሚገኝ መሆኑ የሚያከራክር አይደለም፡፡ በመሆኑም ነው መግለጫው ኦህዴድ ኦህዴድ አልሸት ያለው፡፡

የወያኔ ዋና ችግር የሆነው የድርጅትና የመንግሥት ሥልጣንን እያደበላለቁና እያምታቱ መጠቀም (አንደ አቶ መለስ አባባል የድርጅትና የመንግሥት ኮፍያ ማደበላለቅ) በኦህዴድ መግለጫ በግልጽ ታይቷል፡፡ በመግለጫው የተጠቀሱት ሶስቱም ጉዳዮች የወያኔ ፈቃድ እንደተጠበቀ ሆኖ የክልሉን መንግሥት የሚመለከቱ ናቸው፡፡ ስለሆነም ኦህዴድ እንደ አቶ ጌታቸው ረዳ አገላለጽ የክልሉ ገዥ ፓርቲ ቢሆንም መግለጫውን ማውጣት የነበረበት በድርጅት ወንበሩ ላይ ተሰይሞ ሳይሆን በመንግስትነት መንበሩ ላይ ሆኖ ነው፡፡

ነገር ግን ይህ ባለማወቅ የተደረገ ሳይሆን ወያኔ ሆነ ብሎ የሚጠቀምበት ስልት ነው፡፡ በመግለጫው የተገለጹት ጉዳዮች ታምኖባቸው ሳይሆን ውጥረት ለማስተንፈስና ቁጣ ለማብረድ ካስቻሉ በሚል ስለሆነ በድርጅት እንጂ በክልሉ መንግሥት ስም መገለጽ የለባቸውም አረሳስቶ የፈለጉትን ለማድረግም ሆነ የሚታለል ከተገኘ ሸውዶ ለማለፍ በመንግስት ደረጃ ከመዋሸት በድርጅት መዋሸት ይቀላል፡፡

ኦህዴድ ይህን ከስልጣኑ ውጪ የሆነ መግለጫ ያወጣው የህዝብን ድምጽ የሚሰማ የህዝብ ወገንተኝነት ያለው ድርጅት ስለሆነ ነው የሚሉ ድምጾች ይሰማሉ፡፡ ይህን ለሚሉ ሰዎች ጥያቄው ትክክለኛ መሆኑን ለማወቅና ቁጣ የቀሰቀሰውን ጉዳይ አቁመናል ለማለት ይህን ያህል ግዜ ያስፈልግ ነበር ወይ፤ የጥያቄው ትክክለኝነት የታወቀው በሞቱ በተደበደቡና በታሰሩ ሰዎች ብዛት ነው ወይ፡የሚል ጥያቄ ይኖረናል፡፡እውነታው የሚያሳየው መግለጫውም የሚያረጋግጠው ግን ኦህዴድ በህውኃት ታዞ ምን አልባትም ተጽፎ ተሰጥቶት ያወጣው መግለጫ መሆኑን ነው፡፡

ከመነሻው ኦህዴድ እንደሚለው የኦሮሞ ህዝብ ወኪል፣አሁን አንደተነገረንም የኦሮምያ ጉዳይ የርሱ ጉዳይ በኦሮምያ ክልል ውስጥ ሰላማዊ ተቃውሞ ያሙ ወጣቶችን ከየት እንደመጡና በማን አንደሚታዘዙ የማይታዉቁ ነብሰ ገዳዮች ተሰማርተው ተማሪዎችን በመንገድ ላይ አይደለም እስከማደሪያ ክፍላቸው እየዘለቁ ሲደበድቡ ሲያስሩና ሲገሉ ዝም ማለት ረበት ወይ? ከዚህስ አልፎ ኦቦ ሙክታር የኦሮምያ ክልል ፕሬዝዳንት እየተባሉ ኦሮሞዎችን የገደሉ ነብሰ ገዳዮችን ማመስገን ነበረባቸው? እነዚህና መሰል ድርጊቶች የሚያረጋግጡት ኦህዴዶች የሚሰሩት አይደለም የሚናገሩት ሳይቀረር በወያኔ ትዕዛዝ መሆኑን ነው፡፡

አሁን ኦህዴዶች አጣብቂኝ ውስጥ የገቡ ይመስለኛል፡፡ በርግጥ ወያኔም ይህን ይፈልገዋል፡፡ ይፈልገዋል ብቻም አይደል እንዲሆንም ያደርጋል፡፡በመግለጫቸው የህዝቡ ጥያቄ ትክክል ነው ብለዋል፤በመሆኑም ማስተር ፕላኑ ተግባራዊ እንደማይሆን ተናግረዋል፡፡የተቃውሞው መነሻም መድረሻም ማስተር ፕላኑ ነው ቀርቷል ስንል ተቃውሞውም ይቀራል ከሚል አርቆ ማየት በተሳነው አስተሳሰብ ያወጡት መግለጫ የማይወጡት ችግር ውስጥ የሚከታቸው ፡ካልተወጡት ደግሞ ተቃውሞውን ይበልጥ የሚያባብስ ይሆናል፡፡

የህዝቡ ጥያቄ ትክክል ነው ብለው ያመኑትና ይህን በመግለጫ የገለጹት ኦህዴዶች ከዚህ በኋላ የግድ መመለስ ያለባቸው ለትክክለኛ ጥያቄ የተሰጠው ምላሽ ትክክለኛና ተገቢ ነው ወይ? የሚል ይሆናል፡፡ የቱንም ያህል ነጻነት ባይኖራቸውም፤ አቶ ሙክታር ከድር ገዳዮችን ማወድስ ማመስገናቸውን ባይዘነጋም ኦህዴዶች አንደ ድርጅት የተወሰደው ርምጃ ተገቢና ተመጣጣኝ ነው ለማለት ይደፍራሉ ለማለት ይቸግራል፡፡ ይህ ደግሞ በራሱ አጣብቂኝ ውስጥ የሚያስገባ ነው፡፡ ትክክለኛ ጥያቄ መሆኑን የተረጋገጠለትን ጥያቄ ያነሱ በመቶዎች ተገድለዋል በሺዎች ታስረዋል፣ ግድያውና እስሩ አሁንም አልቆመም፡፡ ይህን ኢሰብአዊ ድርጊት ተገቢና ተመጣጣኝ ርምጃ ነው ካሉ እስካሁን ከፈጸሙት የከፋ በህይወት እስካሉ ድረስ መቼም የማይለቃቸውና አንድ ቀን ለፍርድ የሚያስቀርባቸው ወንጀል በራሳቸው ላይ ጫኑ ማለት ነው፡፡
ርምጃው ተገቢና ተመጣጣኝ አይደልም ካሉ ደግሞ መጀመሪያ የሚገልጹበት መድረክ ላያገኙ ይችላሉ፤ ሁለተኛ ይህን አውነት ለመጋፈጥ ከደፈሩ ከወያኔ ጋር ሆድና ጀርባ መሆናቸው አይቀሬ ነው፡፡ ስለዚህ አስቀድመው ራሳቸውን በመሆን መከላከያቸውን ማዘጋጀት አለያም የሚመጣውን ለመቀበል መሰናዳት ይኖርባቸዋል፡፡ ጥያቄው ግን እዚህ ላይ አይቆምም፡፡ ለትክክለኛ የህዝብ ጥያቄ የተሰጠው ምላሽ ተገቢና ተመጣጣኝ አይደለም ሲባል የሚቀጥለው ግድያ የፈጸሙ፣ የደበደቡ፣ህዝብ የሰደቡና የዘለፉ ለፍርድ ይቅረቡ፤ ለሟች ቤተሰቦች ካሳ ይከፈል የታሰሩ ይፈቱ የሚል ይሆናል፡፡ ኦህዴድ ይህን ተግባራዊ ማስደረግ አይደለም ለመጠየቅ አንኳን አቅምና ነጻነት ይኖረው ይሆን!

የኦህዴድን መግለጫ ተከትሎ የፌዴራሉ መንግሥት ቃል አቀባይ በኦሮምያ ውስጥ የሚሆን ነገር በሙሉ የሚመለከተው የኦሮምያ ገዢ ፓርቲ የሆነውን ኦህዴድን በመሆኑ ውሳኔውን እናከብራለን ብለዋል፡፡ይቺ ጠናማ የምትመስል አነጋገር ከጀርባዋ ትልቅ ሴራ ያላት ትመስላለች፣ በኦሮምያ ለሆነውና እየሆነ ላለው ሁሉ ኦህዴድን ተጠያቂ በማድረግ ህውኃት ራሱን ከደሙ ንጹህ የማድረግ ነገር እሳቤ ሳይኖራት አይቀርም፡፡ መግለጫው በኦሮምያ ክልላዊ መንግሥት ሳይሆን በኦህዴድ እንዲሰጥ የተደረገበት ዋንኛ ዓላማም ይህ ሳይሆን ይቀራል ትላላችሁ፡፡

ከአቶ ጌታቸው አባባል በመነሳት ለህውኃት ጥያቄ ማንሳት ይቻላል፡፡ በኦሮምያ የሚሆነው የሚደረገው ሁሉ የሚመለከተው ኦህዴድን ከሆነ በኦሮምያ ክልል ውስጥ ለተደረገ እንቅስቃሴ ወያኔ ምን ሊያደርግ ዘመተ ? ነው ወይስ ያንግዜ ኦህዴድ መኖሩ አልታያችሁም ነበር?፡ወያኔ ኦሮምያ ዘምቶ የውጪ ወራሪ ሀይል ያስመሰለውን ኢሰብአዊ ድርጊት ፈጽሞ በመቶዎች ገድሎ በሺዎች አስሮ ያሰበውን ማሳካት ሲያቅተው ነው ወይ የኦሮምያ ጉዳይ የኦህዴድ መሆኑ የታየው ?ይህ ወያኔዎቹን ብቻ ሳይሆን ኦህዴዶችንም የሚፈትን ነው፡፡

ስለሆነም በኦህዴድ መግለጫ የተነሳ የተለያዩ ጥያቂዎችን በማንሳት ለወያኔም ለኦህዴድም አጣብቂኙን ማስፋት አያስፈልግም፡፡ ጥያቄው አንድ አጭርና ግልጽ ይሁን፣ ትክክለኛ መሆኑን ላመናችሁትና ላረጋገጣችሁት የህዝብ ጥያቄ የተሰጠው ምላሽ ተገቢና ተመጣጣኝ ነው ወይ ? የሚል፡፡ ከዛ እንደምላሻቸው ከላይ የተነሱት ጥያቄዎች ይቀጥላሉ፡፡ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ውስጥ የሚሰሩ ጋዜጠኞችም ከህውኃትም ሆነ ከኦህዴድ ባለሥልጣናት ጋር ቃለ ምልልስ ሲያደርጉ እዚህ ጥያቄ ላይ ትኩረት ይስጡ፡፡ የህዝቡ ጥያቄ ትክክል ነው የተሰጠው ምላሽስ?
hal-720x445

Advertisements