የራሱን አውሮፕላን የሰራው አስመላሽ ሁለተኛ የበረራ ሙከራውን ሊያደርግ ነው


6dfdf961c172c677b6397c1f4f7009b5_XL
የራሱን አውሮፕላን ሰርቶ ለማብረር ያደረገው ሙከራ ባለመሳካቱ ተስፋ ያልቆረጠው ኢትዮጵያዊ ወጣት አስመላሽ ዘፈሩ የካቲት 11 ቀን 2008 ዓ.ም ሁለተኛ የበረራ ሙከራውን ሊያደርግ ነው።

በቀጣይም ወጣቱ ከግማሽ ሚሊዮን ብር ባነሰ ወጪ አብራሪውን ጨምሮ አራት ሰዎችን የምትይዝ K781H የተሰኘች ሄሊኮፕተር ለመስራት እቅድ እንዳለው ጠቁሟል።

ከተሳካለት በኢትዮጵያም ሆነ በአፍሪካ የመጀመሪያው የአውሮፕላን ፈጣሪ ይሆናል የተባለለት ወጣት አስመላሽ፥ ሰኔ 4 ቀን 2007 ዓ.ም ራሱ በሰራት K570-A አውሮፕላን ሊያደርግ የነበረው የመጀመሪያ የሙከራ በረራ ባጋጠመው የቴክኒክ ችግር ምክንያት መክሸፉ ይታወሳል።

ወጣት አስመላሽ ሁለተኛ የበረራ ሙከራውን አስመልክቶ ዛሬ ለጋዜጠኞች መግለጫ የሰጠ ሲሆን፥ የፊታችን የካቲት 11 ቀን በሚያደርገው የበረራ ሙከራ ላይ የሰርግ ሥነ-ስርዓቱን አብሮ የሚፈጽም መሆኑ ገልጿል።

የአውሮፕላኗ ፈጣሪ ከመጀመሪያ ሙከራው ልምድ በመውሰድ ሁለተኛ ሙከራውን ለማድረግ በአውሮፕላኗ ላይ ማሻሻያዎችን ማድረጉን አስረድቷል።

ከነዚህ ውስጥ አውሮፕላኗን ወደፊት ለመጎተት ወሳኝ የሆነውን ሞተር የመቀየር፣ በመጀመሪያ ሙከራው ችግር ፈጥሮበት የነበረውን የአየር መቅዘፊያ (ፕሮፕላር) ማስተካከል እንዲሁም የክንፎቹን ስፋትና ቁመት መጨመር የሚጠቀሱ ናቸው።

“የመጀመሪያ ሙከራዬን ሳደርግ አውሮፕላኗ የነበራት 40 የፈረስ ጉልበት ያለው አሮጌ የቮልስ ዋገን ሞተር ነበር፤ አሁን በ12 ሺህ ብር ወጪ 78 የፈረስ ጉልበት ያለው የተሻለ ሞተር ነው የተጠቀምኩት፤ በረራዬን ስኬታማ ለማድረግ ተዘጋጅቻለሁ” ብሏል።

ለቀጣይ በረራ የተዘጋጀችው ይህችው አውሮፕላን ከመጀመሪያዋ የተሻለች ከመሆኗም በላይ አገር አቋራጭ ርቀቶችን የመብረር አቅም እንዳላት ነው ፈጣሪዋ የሚናገረው።

በቅርቡ የፈጠራ ስራውን ለመደገፍ ከወጣቱ ጋር የስፖንሰር ሺፕ ስምምነት የተፈራረመው የቻይናው ዜድቲኢ ኩባንያም ለስራዎቹ የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገለት እንደሚገኝ ወጣት አስመላሽ ተናግሯል።

Advertisements