የፌደራሉ የመጀመሪያ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት በመምህር ግርማ ወንድሙ መዝገብ ላይ ፖሊስ በአምስት ቀናት ውስጥ ምርመራውን አጠናቆ እንዲቀርብ የመጨረሻ በሚል ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጠ።


12274630_932515090189604_7558200701177432004_n
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የምርመራ ቡድን ባለፉት ቀናት ባደረገው ማጣራት የጠቅላይ ቤተ ክህነት የፍቃድ ሰነድ በህጋዊ መንገድ አለመሰጠቱን እና መምህር ግርማ ወንድሙ የሚጠቀሙበት ፈቃድ የመስጠት ስልጣን በሌላቸው አካል የተሰጠ መሆኑን አረጋግጠናል ብሏል።
የመስጠት ስልጣን ሳይኖራቸው ፈቃዱን የሰጡት አባትም በሀገር ባለመኖራቸው ተጠያቂ ለማድረግ እሳቸው እስኪመጡ ማህተሙ፣ ፊርማው እና ቲተሩ በማን እንደተዘጋጀ ለማረጋገጥ የፎሬንሲክ ውጤት እየጠበቅን ነው ሲልም ለፍርድ ቤቱ አስታውቋል።
ለዚህም የ14 ቀን ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ ይሰጠን ሲል ጠይቋል።
የመምህር ግርማ ወንድሙ ጠበቆች በበኩላቸው ፍቃድ የሰጠውን አካል ቤተ ክህነት ሊጠይቀው ይገባል እንጂ ደንበኛችን ሊታሰሩ አይገባም ብለዋል።
የፎሬንሲክ ውጤትን በሚመለከትም ፖሊስ በራሱ አጣርቶ ሊያቀርብ ይችላል፤ ውጤቱ ምንም ቢሆን ዋስትናን የሚከለክል ባለመሆኑ የፖሊስ ጥያቄ ውድቅ ተደርጎ የደንበኛችን ዋስትና ይጠበቅልን ሲሉም ጥያቄ አቅርበዋል።
የምርመራ ቡድኑ በበኩሉ ሰነዱ በሌላ አካል ቢሰጥም ተጠርጣሪው ተገልግለውበታል፤ ስለዚህ እሳቸውን ጨምሮ ሌሎች ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር አውሎ መዝገቡን ለማጠናቀቅ ተጠርጣሪው ሳይለቀቁ የጠየኩት የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ይፈቀድልኝ ብሏል።
የፌደራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት የሁለቱንም ወገን ክርክር አድምጦ ለመጨረሻ ጊዜ በሚል የ5 ቀን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፈቅዷል።
በዚህም ተጠርጣሪው በቁጥጥር ስር እንዳሉ ለህዳር 15 ቀን 2008 ዓመተ ምህረት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

Advertisements