ስምንት ዋና ነጥቦች ከእስራኤላውያን (ዮፍታሔ)


Jewish-Ethiopians-Reunited-Families-Israel-o1h5oGhsf2Vlእስራኤላውያን (አይሁድ) በአንድ ወቅት ዛሬ እኛ እንዳጋጠመን የመሰለ ችግር አጋጥሟቸው መፍትሔ ፍለጋ ላይ ነበሩ። ከእኛ ችግር የነርሱ ችግር የከፋም ይመስል ነበር። ሆኖም ያን ችግር ሊፈቱት በቅተዋል። ችግሩን እንዴት ፈቱት? ምናልባት ቢጠቅም 8 ዋና ዋና ነጥቦችን ቀጥለን እንመለከታለን።
Jewish+Ethiopians+Reunited+Families+Israel+o1h5oGhsf2Vlእስራኤላውያን ከ 3000 ዓመት በፊት በግብፅ ወይም ከ2500 ዓመት በፊት በባቢሎን የደረሰባቸው በታሪክ ይታወቃል። ከዚያም ወዲህ ከ2000 ዓመት በፊት በግሪክ ሶርያውያን የደረሰባቸው ታሪክ አለ። በእነዚህ ላይ ተንታኔ ማቅረብ የዚህ ጽሑፍ ዓላማ አይደለም። ከዚያ ወዲህ በሆነው ላይ (እርሱም በጣም ሰፊ ስለሆነ) በወፍ በረር በማተኮር ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ትምህርትና ላለንበት ችግር የመፍትሔ ሐሳብ በሚሆኑት ላይ ብቻ ያጠነጥናል።
ከዚህም በተጨማሪ ይህ ጽሑፍ ከእስራኤላውያን የምንማራቸውን ጠንካራ ነጥቦች እንደምሳሌ ሲያቀርብ ዛሬ እስራኤል በሌሎች ላይ (ቤተ እስራኤላውያንን ጨምሮ) የምታራምደውን ፖሊሲ በጠቅላላ እንደመደገፍ እንዳይታይ ማሳሰብ ያስፈልጋል።
ነገሩ እንዲህ ነው። ቅድመ ልደተ ክርስቶስ 63 (እ. ኤ. አ) ማለትም ከ 2,077 ዓመት በፊት ሮማውያን እየሩሳሌምን በመያዝ ይሁዳን (በጊዜው የእስራኤላውያን መኖሪያ) ተቆጣጥረው እያስገበሩ ሲያስተዳድሩ ቆዩ። ከክርስቶስ ልደት በኋላ እ.ኤ.አ በ 66 ዓ.ም አካባቢ እስራኤላውያን ግፍ ሲበዛባቸው በሮማውያን ላይ አመጹ። ሆኖም ሮማውያን አመጹን በመምታት፣ የእየሩሳሌምን ቤተመቅደስ በማቃጠልና ለጥቂት ዓመታት በኃይል የተቋቋሙዋቸውን አይሁድ በመፍጀታቸው እ.ኤ.አ በ 70 ዓ.ም አብዛኛው አይሁድ አገራቸውን ለቀው ወደውጪ ተሰደዱ። ያልተሰደዱት ደግሞ ከይሁዳና ከእየሩሳሌም ተገፍተው ወጥተው በድንበር አካባቢዎች ይኖሩ ጀመር።
ዛሬ ኢትዮጵያውያን በመላው ዓለም እንደተሰራጨነው አይሁድ የተሰደዱት በጊዜው ወደነበረው ዓለም ይልቁንም ወደአውሮፓ (ጀርመን፣ ፓላንድ፣ ሀንጋሪ፣ ፈረንሳይ፣ ኦስትሪያ፣ ስፔን፣ ራሽያ …)፣ እስያ (ኢራን፣ ኢራቅ፣ የመን) እና ሰሜን አፍሪካ ነበር።
በተሰደዱበት በተለይም በአውሮፓ አይሁድ በመጀመሪያ በባርነት ያገለግሉ እንደነበረ የሚያሳዩ ጥናቶች ይገኛሉ። በሳውዲ አረቢያ እና በሌሎችም የአረብ አገራት ዛሬ በኢትዮጵያውያን እንደሚፈጸምባቸው ዓይነት መሆኑ ነው። እየቆዩ ሲሄዱ ሁኔታዎች የተሻሻሉ መሰሉ። በየሄዱበት ሁሉ አይሁድ ከኗሪው ሕዝብ ጋር ተቀላቀሉ፣ ተጋቡ፣ ተዋለዱ፣ ጥቂት የማይባሉ ሃይማኖታቸውን ቀየሩ፣ ልጆች፣ የልጅ ልጆች ወለዱ። በመጀመሪያ የተሰደዱት በጠቅላላ አልፈው የተወለደበትን አገር አገሬ የሚል እስራኤልን የማያውቅ ትውልድ መጣ። ብዙ ትውልድ አልፎ ብዙ ተተካ።
በዚህ መካከል ግን ወደኋላ ዘራቸው እየተቆጠረና አይሁድ (Jews) ተብለው እየተለዩ በሰበብ አስባብ ጥቃት ይደርስባቸው ጀመር። ይህ ጥቃት በአገራቸው የቀሩትንም አልቀረላቸውም። እ.ኤ.አ በ 1099 “የመስቀል ጦረኞች” እየሩሳሌምን ወረው በሺህ የሚቆጠሩ አይሁዳውያንንና ሙስሊም ፍልስጤማውያንን ገደሉ። እ.ኤ.አ በ1492 የአይሁድ ዝርያ ያላቸው በጠቅላላ ከእስፓኝ ተባረሩ። እ.ኤ.አ በ1791 በሩሲያ የሚኖሩት ከቤት ንብረታቸው ተነቅለው ለብቻቸው ተለይተው እንዲኖሩ ግዞት ተበየነባቸው። ከአንደኛው አገር ጥቃት ሸሽተው የተሻለ ወደመሰላቸው ሌላ አገር ሲሰደዱና ቁጥራቸው ሲበራከት በዚያ በሄዱበት ደግሞ አዲስ ጥቃት ይከፈትባቸው ነበር። በዚህ ዓይነት በፈረንሳይ፣ በጣሊያንና በሌሎችም የአውሮፓ አገራት ጸረ-አይሁድ አዝማሚያዎች ተስፋፉ።
መገፋቱ እየጨመረ ሲመጣ በየከተማው የሚገኙት የአይሁድ ዝርያ ያላቸው (አለን ብለው የሚያምኑ) ግለሰቦች መገናኘትና መሰባሰብ ጀመሩ። የአምልኮ ስፍራዎች (Synagogues) ከሀይማኖትም በተጨማሪ እንደመገናኛና መሰባሰቢያ ማዕከላት ያገለግሉ ጀመር። ሆኖም በየከተማው የሚገኙት የአይሁድ ዝርያ ያላቸው ግለሰቦችና ማኅበራት ጥቃትን አብሮ ለመካፈል ካልሆነ በቀር ጥቃቱን የሚመክቱበት አቅም ከቶም አልነበራቸውም።
በየአገሩ ያሉት አይሁድ የማይተዋወቁና፣ የተለያየ ድብልቅ ዘር፣ ባሕል፣ የኑሮ ዘይቤና የተለያዩ አገራት ሰዎች መሆናቸው ትልቅ ፈተና ሆነ። ይህን አሰባስቦ ዘላቂ የሚሆን የመፍትሔ አቅጣጫ ማግኘት ደግሞ ከዚህም የከበደ ነበር።
ነገር ግን ወረድ ብለን እንደምንመለከተው እነዚህ ከሺህ ዓመታት በላይ በየአገሩ ተለያይተው ይኖሩ የነበሩ ሰዎች ይህን ልዩነትና ታላቅ ፈተና አልፈው ተሰባስበው አገር መመሥረትና በዓለም 16ኛውን ታላቅ የዓለማችን ኢኮኖሚ መገንባት ችለዋል።
በየሄዱበት በተለያዩ ጨካኝ (ነገር ግን ጠንካራ) መንግሥታት ጫና ውስጥ የነበሩና እነርሱ ራሳቸው በብዙ ነገር ተለያይተው የነበሩ አይሁድ አንድ መሆንና ጠንካራ አገር መመሥረት ከቻሉ ሕወኀትን የመሰለ ጠባብና ምንም ዓይነት ሕዝባዊ መሠረት የሌለው ደካማ አገዛዝ አስወግደን ሰው ሰራሽ የሆነውን የእኛን በጎሳ መለያየት አሸንፈን በአንድነት ሁላችንም የምንመኛትን ጠንካራ አገር መገንባት ሊያስቸግረን አይገባም። እንዲያውም የኢትዮጵያን መፍትሔ ከነርሱ ፈጣንና ቀላል ሊያደርገው ይችላል። ነገር ግን በመጀመሪያ ከእስራኤላውያን ተግባራዊ የችግር አፈታት ብዙ የምንማረው ይኖረናል። ወደዚያ ወረድ ብለን እንደርስበታለን።
ችግሩ እየጸና ሲመጣ በየአገሩ ተበታትነው የነበሩት የአይሁድ ዝርያ ያላቸው ማኅበረሰቦች መገናኘት ጀመሩ። እ.ኤ.አ በ 1450 በጀርመን የመጀመሪያው ማተሚያ መኪና (Printing Press) በመሠራቱ ከአንድ ቦታ የሚወጣ ጽሑፍ በሌሎች አገራትም ለሚገኙ የአይሁድ ዝርያ ያላቸው ማኅበራት፣ የአምልኮ ስፍራዎች እና ግለሰቦች ይደርሳቸው ጀመር። ይህ ሁሉ ሆኖ አይሁድ ከተበተኑበት እ.ኤ.አ 70 ዓ.ም ጀምሮ እስከ እ.ኤ.አ 1894 ድረስ (ከ 1800 ዓመታት በላይ) የሚሄዱበት መንገድ የጠፋቸው መስለው ነው የቆዩት ማለት ይቻላል። በዚህ ሰፊ ጊዜ በተናጠል በየቦታው የተሞከሩ ነገሮች ቢኖሩም ለውጤት የበቃና ለሁሉም ተስፋ ሊሆን የሚችል አንድም ፍንጭ አልነበረም።
በ 1894 (እ.ኤ.አ) ግን አንድ አይሁዳዊ ዝርያ ያለው ሀንጋሪያዊ ጋዜጠኛና ደራሲ አንድ ሐሳብ በመጽሐፍ ጽፎ አስራጨ። ይህ ሰው ቴዎዶር ሄርዝል (Theodor Herzel) ይባላል። ያሰራጨው ሐሳብ አዲስ አይደለም። ከርሱ በፊት ሌላ ሰው ጽንሰሐሳቡን ተጠቅሞበታል። ጽዮናዊነት ይባላል። ይህ ስያሜ በኋላ በእስራኤል ተቃዋሚዎች ዘንድ የተለያየ መጥፎ ስም የተሰጠው ቢሆንም ‘ጽዮን’ ከሚለው በእየሩሳሌም ከሚገኝ ተራራ (አምባ) ስም የተወሰደ ነው። ቃሉ ቀድሞውንም አብዛኛው አይሁድ በሚያውቁት የሙሴ መጻሕፍት የሚገኝና ለመላው አይሁዳዊ ለመረዳት ቀላልና ግልጽ የሆነ ቃል ነበር።
“ነገር ግን ዳዊት አምባይቱን ጽዮንን ያዘ፥ እርስዋም የዳዊት ከተማ ናት።” ፪ኛ ሳሙኤል 5፡7
ነገር ግን ቴዎዶር ሄርዝል ዝርዝር መርኅግብርና ስትራቴጂ ነድፎ መጽሐፍ በማሳተም ይህንን ጽንሰሐሳብ የሚታይ፣ የሚጨበጥና የሚያጓጓ ራእይ አደረገው።
የቴዎዶር ሄርዝል ሐሳብ በአጭሩ ይህን ግፍ ለማስቀረት አይሁዳውያን ወደምድራቸው ጽዮን ተመልሰው የራሳቸው አገር መመሥረት ይገባቸዋል የሚል ነው። በዓለማችን ታላቅ ለውጥ ያስከተሉ ሐሳቦችና ሥራዎች ቀላልና ግልጽ የሆኑት ለመሆናቸው ይህ አንድ ሌላ ምስክር ነው። ይህ ሐሳብ በየአገሩ ተበትኖ በበዙ መንገድ ተለያይቶ በነበረው አይሁዳዊ ዝርያ አለኝ ብሎ በሚያምነው ሕዝብ ዘንድ አንድ የጋራ ብሔራዊ መንፈስ ለመፍጠር የታሰበ መሆኑ ግልጽ ነበር። ቴዎዶር ሄርዝል በራሱ በኩል የእምነት ሰው ካለመሆኑም በላይ የጽዮንን (ፍልስጤም) ምድር ከዚያ በፊት ረግጦ አያውቅም።
ሆኖም የቴዎዶር ሄርዝል ሐሳብ ታላቅ ተቃውሞ ገጠመው። ተቃውሞው ደግሞ ከማንም ከሌላ ሳይሆን ከራሱ ወገኖች ከአይሁድ ነበር። ዋናው ምክንያት ከዚያ በፊት ይልቁንም በ 17ኛውና 18ኛው ክፍለዘመን አይሁድ በየሄዱበት ተመሳስለው እንዲኖሩ (ሀይማኖታዊነትን ትተው ዓለማዊ አኗኗርን በመቀበል) ከራሳቸው ወገኖች ግፊት ይደረግ ስለነበረና (“Jewish Enlightenment”) ያም የተሳካ ስለመሰለ አዲሱ ሐሳብ (ሌሎች ምክንያቶች እንደተጠበቁ ሆነው) እንደገና ተመልሰን ተለይተን እንድንታወቅና ለጥቃት እንድንጋለጥ ያደርገናል ከሚል ፍርኀት የመነጨ ነበር። “እግዚአብሔር ለአይሁዳውያን ባዘጋጀው ሐሳብ ላይ (እንደ)ማመጽ” የቆጠሩትም ነበሩ። ተቃውሞው ጠንካራ ከመሆኑ የተነሣ ቴዎዶር ሄርዝል በሙኒክ ሊያደርገው የነበረው የመጀመሪያው ጉባዔ በተቃውሞው ምክንያት ሊሳካ አልቻለም።
ቴዎዶር ሄርዝል ግን በቀጥታ አልቀበል ያሉት ወገኖቹ በተዘዋዋሪ እንዲቀበሉት ለማድረግ ከእንግሊዝ፣ ጀርመን፣ ፖላንድና ቱርክ ታላላቅ ሰዎች ጋር በየመድረኩ እየታየና በጥቂት ግለሰቦች ተግባራዊ ርዳታ እየተደረገለት ጥረቱን አላቋረጠም። በዚህም መሠረት እ.ኤ.አ በ1897 የመጀመሪያውን የአይሁድ ዓለም-አቀፍ ጉባኤ (Zionist Congress) በአብዛኛው በራሱ ወጪ በቤዝል (Basel) ስዊትዘርላንድ አካሂዶ በኋላ የዓለም ጽዮናዊነት ድርጅት (World Zionist Organization) በሚል የተሰየመው ድርጅት ሊመሠረት በቃ። የርሱ እቅድ እስራኤልን በቶሎ (1923 እ.ኤ.አ) ለመመሥረት የነበረ ቢሆንም የራሱ ወገኖች ተቃውሞ፣ ማመንታት፣ ሐሳቡን ለመቀበል መዘግየታቸውና እንግሊዝና ሌሎችም ሁኔታዎች የፈጠሩት መጓተት አይሁዳውያንን በአንደኛው የዓለም ጦርነትና ይልቁንም በሁለተኛው የዓለም ጦርነት አያሌ የሕይወትና የንብረት ዋጋ አስከፍሏቸዋል።
ምንም እንኳን በዚህ ወቅት በፍልስጤም የሚኖሩ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ አይሁዳውያን ቢኖሩም ይህ ድርጅት በዳያስፖራው የተቋቋመ እንደመሆኑ (መስራቾቹም በአብዛኛው በጊዜው በጀርመን የነበሩት አይሁድ ስለነበሩ) ጽ/ቤቱን በበርሊን አደረገ። ይህ ድርጅት ለእስራኤላውያን በኋላ ያደረገውንና እስራኤልንም እስከመመሥረት እንደበቃ ስንመለከት ይህን የተቃወሙትን ሰዎች ሁሉ የሚያሳፍር እንደነበረ አይጠረጠርም። ይህ ወደመጀመሪያው ትምህርታዊ ነጥብ ይወስደናል።
ድርጅት፣ ድርጅት፣ ድርጅት፤ ተቋማት፣ ተቋማት፣ ተቋማት።
(ክፍል 2 ይቀጥላል)

ኢትዮጵያ በቆራጥ ልጆቿ ሥራ ታፍራና ተከብራ ለዘለዓለም ትኖራለች!

Advertisements