በጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ላይ የተወሰነው የጽኑ እስራት ውሳኔ ተገቢ አይደለም ተባለ


‹‹በመጻፉና በመናገሩ አንድም የተከሰሰና የታሰረ ጋዜጠኛ የለም›› መንግሥት

temesgen2_330_228የፍትሕ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅና የፋክት መጽሔት ዓምደኛ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ፣ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 9ኛ ወንጀል ችሎት፣ ጥቅምት 17 ቀን 2007 ዓ.ም. የወሰነበትን የሦስት ዓመታት ጽኑ እስራት ተከትሎ፣ ጋዜጠኞችን በእስራት መቅጣት በሕገ መንግሥቱ የተፈቀደውን የመጻፍና የመናገር መብት መጣስ መሆኑን ጠበቃ አመሀ መኮንን ገለጹ፡፡

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በ2004 ዓ.ም. ነሐሴ ወር መጀመሪያ ሳምንት አካባቢ፣ በፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ክስ ተመሥርቶበትና ዋስትና ተከልክሎ ለአንድ ሳምንት ያህል በማረሚያ ቤት ከቆየ በኋላ፣ ዓቃቤ ሕግ ‹‹የማጣራው ነገር ስላለኝ ለጊዜው ክሴን አቋርጫለሁ›› በማለቱ ከእስር መፈታቱ ይታወሳል፡፡

የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ በድጋሚ የጋዜጠኛ ተመስገንን ክስ ሲያንቀሳቅስ፣ ይዟቸው የቀረበው ክሶች፣ የወንጀል ሕግ 257(ሀ)ን በመተላለፍ በፍትሕ ጋዜጣ ላይ አመፅ የሚቀሰቅሱ ጽሑፎችን በራሱና በሌሎች አመንጭነት እንዲታተሙ ማድረጉን፣ የወንጀል ሕግ 244ን በመተላለፍ የመንግሥትን ስም የሚያጠፉና በሐሰት የሚወነጅሉ ጽሑፎችን እንዲታተሙ ማድረጉን እንዲሁም የወንጀል ሕግ 486 (ሀ)ን በመተላለፍ የሕዝብን ስሜት የሚያናውጡ ጽሑፎች እንዲታተሙ ማድረጉን የሚገልጹ ሲሆን፣ ዓቃቤ ሕግ ‹‹አሻሽላለሁ›› ብሎ ክስ ያቋረጠ ቢሆንም፣ ክሶቹ ግን ቀድሞ የመሠረታቸው መሆናቸውን የክስ ሰነዱ ያስረዳል፡፡

በጋዜጠኛው ላይ የተመሠረቱት ክሶች የሚያስረዱት፣ ጋዜጠኛው የተከሰሰው በጻፈውና እንዲታተሙ ባደረጋቸው መጣጥፎች ከመሆኑ አንፃር፣ መንግሥት በተለያዩ ጊዜያት ‹‹አንድም ጋዜጠኛ በጻፈውና ባተመው ጽሑፍ አይከሰስም፤ ተከሶም አያውቅም›› የሚለውን የመንግሥት መግለጫ የሚቃረን ተግባር መፈጸሙን የጋዜጠኛ ተመስገን ጠበቃ አቶ አመሀ ተናግረዋል፡፡

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሟቹ አቶ መለስ ዜናዊና የእሳቸው ምትክ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ሳይቀሩ የተናገሩትና እየተናገሩ ያሉት፣ ‹‹በኢትዮጵያ ውስጥ ፍርድ ቤት የሚቀርቡና እስራትም የተወሰነባቸው ጋዜጠኞች ያሉ ቢሆንም፣ በጻፉት ጽሑፍ ሳይሆን፣ ሥራቸውን ከለላ በማድረግ ተገቢ ባልሆነ ወንጀል ውስጥ ሲሳተፉ በመገኘታቸው ነው፤›› ማለታቸውን ያስታወሱት አቶ አመሀ፣ የባለሥልጣናቱ ንግግር የተወሰነ ተቀባይነት ያለው መከራከሪያ ቢሆንም፣ በተመስገን ላይ የሆነው ግን የባለሥልጣናቱን ንግግር ሙሉ በሙሉ ውድቅ የሚያደርግና የተጣረሰ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በመንግሥት በኩል ሐሳብን በነፃነት ከመግለጽ መብት አንፃር የአቋም ለውጥ እየተደረገ ነው የሚል ጥርጣሬ እንዳደረባቸው የሚናገሩት ጠበቃ አመሀ፣ ጋዜጠኛም ሆነ ሌላው የኅብረተሰብ አካል፣ በጽሑፍም ሆነ በማንኛውም መንገድ ሐሳቡን ቢገልጽ ክስ ሊቀርብበትና የእስር ቅጣት ሊወሰንበት የሚችልበት ሁኔታ ይፈጠራል የሚል ሥጋት እንዳሳደረባቸው ገልጸዋል፡፡

ጋዜጠኛ ተመስገን በሁለተኛነት የቀረበበት ክስ፣ የወንጀል ሕግ 244ን በመተላለፍ በጻፋቸው ጽሑፎች የመንግሥትን ስም ማጥፋቱንና በሐሰት መወንጀሉን የሚገልጹ መሆናቸውን የጠቆሙት አቶ አመሀ፣ ‹‹አንድ ሰው ሐሳቡን ሲገልጽ መቼ ነው የመንግሥትን ስም የሚያጠፋው? በሐሰት የሚወነጅለው? ይኼ መለኪያ የሚኖረው ነገር አይደለም፤›› ብለዋል፡፡

አንዱ የዴሞክራሲ መገለጫ ነጥብ መንግሥትን መተቸት መሆኑን፣ ተችው አካል ባለው ግንዛቤ፣ አቅምና ቋንቋ መሠረት መተቸት መሆኑን የጠቆሙት ጠበቃው፣ ትችቱ ተገቢ ካልሆነ መንግሥትም ሆነ ሌላ አካል ‹‹ትክክል አይደለም›› ብሎ አስተያየት ከመስጠት ባሻገር፣ መንግሥት ትችት በቀረበበት ጊዜ ያለምንም መለኪያ ‹‹ስሜ ጠፍቷልና፣ ተተችቻለሁ›› እያለ ሕግ አስከባሪ ተቋሙን በመጠቀም፣ ክስ የሚመሠርትና የሚያስቀጣ ከሆነ አደገኛ አካሄድ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

ጋዜጠኛ ተመስገን የመሠረቱበት ከላይ የተጠቀሱት ሦስት ክሶች ላይ ዓቃቤ ሕግ በፍትሕ ጋዜጣ ላይ የወጡትን መጣጥፎች ብቻ በማስረጃነት ሲያቀርብ፣ ተከሳሽ ተመስገን፣ ለክሱ መቃወሚያ ቢያቀርብም ፍርድ ቤቱ የክስ መቃወሚያውን ውድቅ በማድረግ የእምነት ክህደት ቃል እንዲሰጥ አድርጎታል፡፡ ‹‹ወንጀል አልፈጸምኩም፤ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ ሕገ መንግሥታዊ መብቴን ነው የተጠቀምኩትና መረጃ ያስተላለፍኩት፤›› በማለት የእምነት ክህደት ቃሉን ሰጥቷል፡፡ ፍርድ ቤቱም የዓቃቤ ሕግን የጽሑፍ ማስረጃ መርምሮ እንዲከላከል ብይን ሰጥቶበት ነበር፡፡

ጋዜጠኛ ተመስገን በጠበቃው አቶ አመሀ መኮንን አማካይነት ክርክሩን ያደረገ ሲሆን፣ ለመከላከያ ማስረጃነት ዶ/ር ያሬድ ለገሰና ጋዜጠኛ እንዳልካቸው ኃይለ ሚካኤል የተባሉ የሙያ (Experts) ምስክሮችን፣ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያምን ደግሞ በፍሬ ነገር ምስክርነት አቅርቦ አሰምቷል፡፡

ዓቃቤ ሕግ የሙያ ምስክሮችን በመቃወም ለፍርድ ቤቱ አቤቱታ ያቀረበ ቢሆንም፣ ፍርድ ቤቱ የዓቃቤ ሕግን ተቃውሞ ውድቅ በማድረግ የሙያ ምስክሮቹ እንዲሰሙ ፈቅዷል፡፡ በሕገ መንግሥትና ሐሳብን በነፃነት በመግለጽ ዙሪያ በርካታ ምርምሮችን በማድረግና ግኝታቸውን በተለያዩ ከፍተኛ ስብሰባዎች ላይ በመገኘት ማብራሪያ የሚሰጡ ከፍተኛ ባለሙያ መሆናቸው የተነገረው ዶ/ር ያሬድ ለገሰ፣ ጋዜጠኛ ተመስገን በዋና አዘጋጅነት ይሠራበት በነበረው ፍትሕ ጋዜጣ ላይ ያተማቸውንና ለክስ ያበቁትን ጽሑፎች ማየታቸውን በመግለጽ አስረድተዋል፡፡

አመፅን በመስበክና አመፅን በመቀስቀስ መካከል ሰፊ ልዩነት እንዳለ ጠቁመው፣ በጋዜጣው ላይ የታተሙት መጣጥፎች አመፅን ከመስበክ ያላለፉና የአመፅ ቀስቃሽነት ባህሪ እንደሌላቸው ተናግረዋል፡፡

ከጋዜጠኝነት ሥነ ምግባር አንፃር በፍትሕ ጋዜጣ ላይ የታተሙትን መጣጥፎች መመርመራቸውን የገለጹት ሁለተኛው የሙያ ምስክር ጋዜጠኛ እንዳልካቸው ኃይለ ሚካኤል ሲሆኑ፣ ጋዜጠኛ ወገንተኛነቱ ለሕዝብ መሆኑንና መረጃ የማድረስም ኃላፊነት ያለበት ከመሆኑ አንፃር፣ በጋዜጣው ላይ የታተሙት መጣጥፎች ከጋዜጠኛነት አንፃር ችግር እንደሌለባቸው አስረድተዋል፡፡ የሙያ ምስክሮቹ ለፍርድ ቤቱ ከሰጡት ሰፊ የሙያ ምስክርነት ቀጥሎ የፍሬ ነገር ምስክር ሆነው የቀረቡት ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ናቸው፡፡

በተለይ ሁለተኛ ክስ ላይ የመንግሥትን ስም ማጥፋትና በሐሰት መወንጀል በሚመለከት ፕሮፌሰሩ ሲያስረዱ፣ እሳቸው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ ሊቀመንበር በነበሩበት ጊዜ፣ በኢትዮጵያ የተፈጸሙትን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች በሚመለከት በባለሙያ እየታገዙና፣ ድርጊቶች በተፈጸሙበት ቦታ እየተገኙ ደረጃውን የጠበቀ ምርመራ በማድረግ፣ የሚያወጧቸውን ሪፖርቶች ከፓርላማ ጀምሮ ለሚመለከተው ሁሉ ያሰራጩ እንደነበር ገልጸው፣ ጋዜጠኛ ተመስገን ያተማቸው መጣጥፎች የመጀመሪያ ጊዜ እንዳልሆኑ አስረድተዋል፡፡

ዓቃቤ ሕግ በክስ ዝርዝሩ ውስጥ በወቅቱ በዓረብ አገሮች የነበረውን ዓይነት አመፅ እንዲቀሰቀስ ለማድረግ በማሰብ የሚለውን በሚመለከት፣ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ‹‹በኢትዮጵያ ውስጥ በዓረቡ ዓለም የታየውን ዓይነት አመፅ ሊፈጸም የሚችልበት ምንም ዓይነት ተጨባጭ ሁኔታ የለም፤›› በማለት የተናገሩትንና በአዲስ ዘመን ጋዜጣ የታተመውን የሰነድ ማስረጃ፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ ያሳተማቸውን ሪፖርቶች፣ አምኒስቲ ኢንተርናሽናል በበደኖና አርባጉጉ የነበረውን ግድያ የሚያመለክት ያወጣውን ሪፖርት ጨምሮ በርካታ የጽሑፍ ማስረጃዎችንም አቅርቦ ነበር፡፡

ፍርድ ቤቱ፣ የተከሳሹ መከላከያ ምስክሮችና የሰነድ ማስረጃዎች፣ የዓቃቤ ሕግን ክስ ሊያስተባብሉ እንዳልቻሉ በመናገር፣ ጥቅምት 5 ቀን 2007 ዓ.ም. በሦስቱም ክሶች ጥፋተኛ ብሎታል፡፡ ከ12 ቀናት የማረሚያ ቤት ቆይታ በኋላ፣ ጥቅምት 17 ቀን 2007 ዓ.ም. ጋዜጠኛ ተመስገን ጥፋተኛ በተባለባቸው ሦስት ክሶች ቅጣት ለመስማት ፍርድ ቤት የተገኘ ቢሆንም፣ የወንጀል ሕግ 257 (ሀ)ን ተላልፏል በተባለበት በአንደኛው የወንጀል ክስ ብቻ፣ የሦስት ዓመታት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ተወስኗል፡፡ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝም ወደ ማረሚያ ቤት ተጉዟል፡፡ የፍትሕ ጋዜጣ አሳታሚና በክሱ ተካቶ የነበረው ማስተዋል የሕትመትና ማስታወቂያ ድርጅት ዓቃቤ ሕግ በ50 ሺሕ ብር እንዲቀጣ የቅጣት ማክበጃ ያቀረበበት ቢሆንም፣ ፍርድ ቤቱ በ10 ሺሕ ብር እንዲቀጣ ወስኗል፡፡ ዓቃቤ ሕግ በተመስገን ላይ ያቀረበው የቅጣት ማክበጃ እንደሌለም ተገልጿል፡፡ ጋዜጠኛ ተመስገንም የቅጣት ማቅለያ አላቀረበም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ጥፋተኛ መባሉን ካለመቀበሉም በተጨማሪ፣ ጥፋተኛ መባል እንደሌለበትም በማመኑና ፍትሕ እንዳለ እንደማይሰማው ስለሚያምን መሆኑን በጠበቃው አቶ አመሀ መኮንን በኩል ገልጿል፡፡
Source:: Ethiopian Reporter

Advertisements