‹የሚዲያ ካውንስል እንደ ወንፊት እንክርዳዱን ለመለየት ያገለግላል››


a8f687e2d9a2b8d72ee44f9993accfa2_XL

ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት ትምህርት ቤት ተባባሪ ዲን

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የሚዲያ ኢንዱስትሪ ውስጥ ተዋናይ የሆኑ የሚዲያ ተቋማት ለረዥም ዓመታት ሲጠበቅ የነበረውን የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት (ካውንስል) ለመመሥረት የመጨረሻው ደረጃ ላይ ሰሞኑን

መድረሳቸው ይታወቃል፡፡ ይህ የሚዲያ ካውንስል ጐርባጣ የሆነውን የኢትዮጵያ የሚዲያ ኢንዱስትሪ በማስተካከል ረገድ ምን ዓይነት ሚና ሊኖረው ይችላል በሚሉ ጉዳዮችና ሌሎች የኢትዮጵያ ሚዲያ ታሪካዊ ዳራዎችን በማንሳት፣ ዮሐንስ አንበርብር የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት ትምህርት ቤት ተባባሪ ዲን ከሆኑት ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ ጋር ያደረገው ቆይታ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃን ኢንዱስትሪ ሁኔታን እንዴት ይመለከቱታል?

ዶ/ር ነገሪ፡- የኢትዮጵያ ሚዲያ በተለይ ባለፉት ሁለት አሠርት ዓመታት ውስጥ ሁለት የተቀላቀሉ ነገሮች ገነው የታዩበት ነው፡፡ በአንድ በኩል ከፍተኛ ችግሮች በሚዲያው ውስጥ ነግሠው የታዩበት፣ በሌላ በኩል ሚዲያው ባለፉት ሁለት አሠርት ዓመታት ውስጥ ከፍተኛ ዕድገትም ያሳየበት ነበር ማለት ይቻላል፡፡ የኢትዮጵያ ሚዲያ በባዶ ወይም በቫኪዩም ላይ የተመሠረተ አይደለም፡፡ ባለፉት 20 ዓመታት ውስጥ የተመሠረተም አይደለም፡፡ የራሱ ታሪካዊ አመጣጥና ታሪካዊ ‹‹ሌጋሲ›› አሁን ባለው የሚዲያ ኢንዱስትሪ ላይ ተፅዕኖ ማድረጉ አልቀረም፡፡

በንጉሡ ጊዜ የነበረው የኢትዮጵያ ሚዲያ ንጉሡንና የንጉሡ ባለሥልጣናትን የሚያሞግስ ነበር፡፡ በመርህ ደረጃም ተገድቦ 25 የተዘረዘሩ ጉዳዮችን ሚዲያው በትኩረት እንዲዳስስ የተገደደበት ነበር፡፡ የሌላውን አገር የፖለቲካ አመለካከትና የኢኮኖሚ ሁኔታ መዘገብ አይቻልም ነበር፡፡ ጥሩ ያልሆኑ ማኅበራዊ ቀውሶችንና በወቅቱ ሲስፋፉ የነበሩትን እንደ ሴተኛ አዳሪነት የመሳሰሉትን መዘገብ አይቻልም ነበር፡፡ በደርግ ጊዜም ቢሆን ጥሩ የሚባል የሚዲያ ኢንዱስትሪ ታሪክ የለም፡፡ የወቅቱ ወታደራዊ መንግሥት ፖለቲካዊ አመለካከት የሆነውን የኮሙዩኒስት ማኑፌስቶ ብቻ ለሕዝቡ እንዲያሰርፁ አጠቃላይ የሚዲያዎቹ ሥራ ፕሮፓጋንዳ እንደነበር ከታሪካቸው መረዳት ይቻላል፡፡ ስለዚህ በሁለቱ መንግሥታት ዘንድ ነፃ ሚዲያ አልነበረም ማለት ነው፡፡ ወደ ኢሕአዴግ መራሹ ሥርዓት ስንመጣ የተለየ ነው፡፡ ኢሕአዴግ ሥልጣን በያዘበት ወቅት በ1980ዎቹ ሦስተኛው የዲሞክራሲ ሞገድ አፍሪካ ላይ መንፈስና መስፋፋት ጀምሮ ነበር፡፡

በመሆኑም ኢሕአዴግ ሥልጣን በያዘባቸው ዓመታት ይህ የዲሞክራሲ ንፋስ ኢትዮጵያ ላይም መንፈስ ጀምሮ ነበር፡፡ ስለዚህ ይህንን ዲሞክራሲያዊ ሒደት ከመቀበል ውጪ አማራጭ አልነበረውም፡፡ ዲሞክራሲ የራሱ ባህሪያት አሉት፡፡ ከእነዚህ መካከል ደግሞ የነፃ ሚዲያ መስፋፋት አንዱ ነው፡፡ አንድ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እዘረጋለሁ የሚል መንግሥት ነፃ ሚዲያን አግልሎ ወይም ሳያስፋፉ ዲሞክራሲያዊ ነኝ ማለት ስለማይችል በሕግ የሚዲያ ነፃነት በኢትዮጵያ ተፈቀደ፡፡ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ነፃ ሚዲያ አስፈላጊ መሆኑን፣ እንዲሁም ነፃ ሚዲያ ነፃ ሆኖ መሥራቱ መረጋገጥ አለበት የሚለውን ጽንሰ ሐሳብ ተቀብሎ የሕጉ አካል አድርጐታል፡፡ ስለዚህ ስለነፃ ሚዲያና ስለፕሬስ ሕግ መናገር የጀመርነው ከ1980ዎቹ በኋላ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የነፃ ሚዲያ ጽንሰ ሐሳብንና መርህን በወቅቱ ኢትዮጵያውያን እንዴት ተቀበሉት? ይህንን የዲሞክራሲ አንድ ገጽታ ተቀብሎ በአግባቡ የመተርጐም አቅም ነበር?

ዶ/ር ነገሪ፡- ዲሞክራሲ ኢትዮጵያ ውስጥ የመጣው ከኅብረተሰቡ አይደለም፡፡ ዲሞክራሲ ከላይና ዲሞክራሲ ከታች (Democracy from Above Democracy from Below) የሚባሉ አመለካከቶች አሉ፡፡ ከዚህ አንፃር ኅብረተሰቡ ስለዲሞክራሲ ግንዛቤ ኖሮት ከራሱ ያመጣው ባህል አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ሥርዓት ለመቀየር የተነሱ ታጋዮች ባገኙት ድል ነው ዲሞክራሲ ከላይ ወደ ታች የወረደው፡፡ ሕዝቡ እንዴት ተቀበለው ስንል የዲሞክራሲ ባህልን አውቆ ለመቀበል ዝግጁ ስላልነበረ፣ ኅብረተሰቡ በአጠቃላይ የተከፋፈለ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ታሪካዊ የሕዝቦች መከፋፈል መጨቋቆንና የተበላሸበት ሁኔታ ነበር፡፡ ሥርዓቱ ስለማይፈቅድላቸው ነው እንጂ ቂም ይዘው ሲጓዙ የነበረበት አጋጣሚ ነበር፡፡

በአጠቃላይ ኢሕአዴግ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ብሎ ሲመጣ ምቹ ሁኔታ አልነበረም ማለት ነው፡፡ ፅንፈኛ የፖለቲካ አመለካከቶች ነበሩ፡፡ በዚህ ውስጥ ሕዝቡ ነፃ ሚዲያን በተገቢው መንገድ ተቀብሎ ይተረጉመዋል ማለት አይቻልም፡፡

በዚህ ሁኔታ ውስጥ የተጀመረው የኢትዮጵያ ነፃ ሚዲያ ሙያዊ ሥነ ምግባሩን ይዞ እንደ ሙያ መቀጠል አልቻለም፡፡ የተለያዩ ቡድኖች ለኢትዮጵያ ይኼ መንገድ ነው የሚበጀው እያሉ እያንዳንዱ ቡድን የየራሱን ሐሳብ የሚያቀርብበት ነበር፡፡ ነገር ግን መግባባት አልነበረም፡፡ ዲሞክራሲ ውስጥ ደግሞ መግባባት አስፈላጊና ወሳኝ ነው፡፡ በዚህ አለመግባባት የተነሳ የሚዲያው ልዩነትም እየሰፋ መጣ፡፡ መንግሥት የራሱን ሚዲያ ማጠናከር ጀመረ፡፡ ሌላው ደግሞ ሌሎቹን ነፃ ሚዲያ የተባሉትን በወቅቱ መጠቀም ጀመሩ፡፡ በአጠቃላይ የነፃ ሚዲያ እሴቶች ያልነበረበት አጀማመር ነው የታየው፡፡ ነፃ ሚዲያ ማለት እኮ ኃላፊነት ያለበት ነው፡፡ ነገር ግን ከጋዜጠኝነት ሙያም ወጥተው ሲዘግቡ የነበረበትን ጊዜ እናስታውሳለን፡፡ ይህንን ያመጣው የርዕዮተ ዓለም ልዩነት ነው፡፡ ኢትዮጵያን እንዴት ነው የምንገነባው የሚል፡፡ በዚህ ላይ መግባባት ስላልነበረ ፖለቲካው ፅንፍ ወጣ፡፡ ይህንን ተከትሎም ሚዲያው የተለያዩ ሐሳቦችን ለማራመድ ጽንፍ ወጣ፡፡

በጣም ትልቅ ችግር የነበረው ሚዲያው ሙያው የሚፈቅድለትን በመተግበር ትክክለኛ የሆነ የሚዲያ ውጤት ለሕዝብ ሲያደርስ አልነበረም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ መንግሥት አደጋ እንደሚፈጥሩበት በማሰብ ዕርምጃ ሲወስድ ነበር፡፡ የሚወስደው ዕርምጃ ደግሞ በሚዲያ መብት ጉዳይ ለሚሠሩና ለዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡ ኢትዮጵያን ለመፈረጅ እንደ ግብዓት ያገለግል ነበር፡፡ ጦርነት ያመጣው የኢኮኖሚና የፖለቲካ አመለካከት ሳይረጋጋ ሚዲያው ደግሞ እንደገና የራሱን ግንባር ይዞ መምጣቱ፣ መንግሥትም ደግሞ በራሱ ዝግጁ ስላልነበረ ይህም ማለት የዴሞክራሲ ተቋማት ባለመኖራቸው ሚዲያው ከእነዚህ ችግሮች ጋር ነው የዘለቀው ማለት እንችላለን፡፡ በተለይ በመጀመሪያዎቹ አሠርት ዓመታት በአጠቃላይ የፖለቲካ ፍጥጫ መድረክ እንጂ ነፃ ሚዲያ ማለት አስቸጋሪ ነው፡፡

ጋዜጠኞች ሥልጣን የተሰጣቸው እውነት ተናጋሪዎች (Authorized truth teller) ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ሚዲያ ላይ ያለውን ይዘት ስንመለከተው ግን ይህንን ማየት አይቻልም፡፡ እነዚህን ፈተናዎች አልፈው የወጡና አሁንም የሚዲያ ሥራው ላይ ከፍተኛ ተዋናይ የሆኑ አሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ ውስብስብ የሚዲያ ከባቢ እንዲፈጠር መንግሥት የራሱ ድርሻ የለውም ወይ? ለምሳሌ አፋኝ የሚባሉ ሕጐችን ማውጣቱና ሽብርተኝነትን ለመዋጋት ሲባል የተደነገገው አዋጅ ሽብርተኝነትን ሳይሆን ሚዲያውን አልተዋጋም ወይ?

ዶ/ር ነገሪ፡- የእኔ ምልከታ ምንድን ነው? አንዳንድ ሰዎች በኢትዮጵያ የሽብር ሥጋት የለም፣ ስለዚህ ሕጉ አያስፈልግም የሚሉ አሉ፡፡ እኔ ይህንን ለመወሰን የፖለቲካ ተንታኝ አይደለሁም፡፡ ነገር ግን ሁኔታዎችን ስመለከት በምሥራቅ አፍሪካ የሽብር ሥጋት በወቅቱ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ፍንትው ብሎ እየተመለከትነው ነው፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ሕጐች የፀረ ሽብር አዋጁም ሆነ ሌሎቹም ውስንነቶች አሉዋቸው፡፡ ይህ ማለት ያልተፈለገ ትርጉም ተሰጥቶት መንግሥትም ሆነ ሌላም አካል የፈለገውን ውሳኔ እንደሚሰጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ የታወቀ ነው፡፡ ይህ ማለት ግን ተገቢ ነው ማለት አይደለም፡፡ የፀረ ሽብር ሕጉ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ሚዲያውን ለማፈን መጠቀም አይቻልም ብዬ መደምደም አልችልም፡፡ እንደ አንድ ባለሙያ ሥልጣን ያለው አካል ያንን ሕግ በራሱ ትርጓሜ ተጠቅሞ የፈለገውን ማድረግ ይችላል፡፡ ዋናው ነገር ነፃ የሆነ ሕግ ተርጓሚ ካለ አልቀበልም ማለት ይቻላል፡፡ የተከሰሱ ሰዎች ይለቀቃሉ፡፡ በአንዳንድ ጉዳዮች ፍርድ ቤቶች ይህንን አላደረጉም ማለት አይቻልም፡፡

በሌላ በኩል የፀረ ሽብር ሕጉ ጋዜጠኞችን መሠረት አድርጐ ነው እንዴ የወጣው? የሚለውን መጠየቅ አለብን፡፡ ነገር ግን ሕጉ ጋዜጠኞችን ሥጋት ውስጥ አልከተተም፣ እንዲሁም ራስን ሳንሱር ወደ ማድረግ አልከተተም ማለት አልችልም፡፡ ሳንሱር በሕግ የተከለከለ ቢሆንም በፀረ ሽብር ሕጉ ሳቢያ ግን ጋዜጠኞች ከፍተኛ ወደሆነ ራስን ሳንሱር ማድረግ ውስጥ ገብተዋል፡፡ ግን ሕጉ አያስፈልግም ማለት አይቻልም፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ሚዲያ ያለፈበትን ሙሉ ሥዕል በደምሳሳው ገልጸውልኛል፡፡ አሁን ከእነዚህ ሁሉ ዓመታት በኋላ የኢትዮጵያ ሚዲያ ኢንዱስትሪ ተዋናዮች ራሳችንን በራሳችን እንቆጣጠራለን ከሚል መርህ በመነሳት፣ የመገናኛ ብዙኃን ካውንስል (Media Council) እያቋቋሙ ነው፡፡ ይህንን እንዴት ያዩታል?

ዶ/ር ነገሪ፡- ቀደም ብሎ የተመለከትናቸው ችግሮች መሠረታዊ ምክንያታቸውን ተነጋግረናል፡፡ እንግዲህ ጥሩ መሠረት የሌለው የሚዲያ ኢንዱስትሪ ለሁለት አሠርት ዓመታት ይዘን እዚህ ደርሰናል፡፡ አሁን የካውንስሉ መመሥረት ከመንግሥት ጋር መላተምና በየጊዜው ከመከሰስ የተሻለ ሁኔታን ይፈጥራል ብዬ አስባለሁ፡፡ ካውንስሉ ቢመሠረት መጀመሪያ ተጠቃሚ የሚሆነው የትኛውም ዓይነት መንግሥት ይፈጠር የኢትዮጵያ መንግሥት ነው፡፡ ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመፍጠር የሚሠራ መንግሥት የሚዲያ ካውንስል መፈጠሩ ይረዳዋል፡፡ አላስፈላጊ ክስ ከመመሥረት ይረዳዋል፡፡

በዴሞክራሲያዊ አገር ውስጥ የሚዲያ ነፃነት አለ፡፡ በተመሳሳይም የሚዲያ ኃላፊነትም አለ፡፡ ይህንን ኃላፊነት በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ እያስጠበቀ የሚገኘው መንግሥት ነው፡፡ ነገር ግን በተለይ በዲሞክራሲያዊ መንግሥት ውስጥ እነዚህን የሚዲያ ኃላፊነቶች የማስጠበቅ ግዴታ የመንግሥት መሆን የለበትም፡፡ የተቋማት ነው መሆን ያለበት፡፡ እነዚህ ተቋማት ደግሞ የግድ የመንግሥት መሆን የለባቸውም፡፡ እንደ ሚዲያ ካውንስል ያሉ ተቋማት በኢትዮጵያ ቢስፋፉና ሥር ቢይዙ የመንግሥትን ትልቅ ጥያቄ የሚመልስ ነው፡፡ ሕዝቡ ትክክለኛ መረጃ እንዲያገኝ ይረዳል፡፡ የጋዜጠኝነት ሙያ እንዲከበር ያደርጋል፡፡ በኢትዮጵያ የሚዲያ ነፃነት እንዲጠበቅ ዘብ ይሆናል፡፡ የሚዲያ መስፋፋት ሊኖር የሚችለው የሕዝብ ዕውቅና ሲያገኝ ነው፡፡ ሕዝቡ ደግሞ እውነተኛ መረጃ ይፈልጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ የሚዲያ ካውንስል ትልቅ ሚና ይኖረዋል፡፡ አላስፈላጊ ከሆነ ራስን ሳንሱር ማድረግ እንዲቀር አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡ ጋዜጠኞች በኢትዮጵያ የፍትሕ አካል ላይ እምነት እንዲኖራቸው ያደርጋል፡፡

ይህንን ያልኩበት ምክንያት እኔም ሆነ ሌሎች ባለሙያዎች ባካሄድነው ጥናት ጋዜጠኞች (የመንግሥትም ሆነ የነፃ ሚዲያው ጋዜጠኞች) በፍርድ ቤቶች ላይ እምነት የላቸውም፡፡ ነፃ አይደለም፣ አይከላከልልኝም የሚል እምነት አላቸው፡፡ የእኔን እውነት ለመጠበቅ ሳይሆን ለመንግሥት ነው የሚሠራው የሚል እምነት አላቸው፡፡ ይህ ሁልጊዜ እውነት ነው ብሎ መደምደም ባይቻልም የእነሱ እምነት ግን ቀላል አይደለም፡፡ ለፍትሕ አካሉ ያላቸው አስተሳሰብ በራሱ በጋዜጠኝነት ሙያ ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል፡፡ ካውንስሉ ቢመሠረት ይህንን ሁሉ መከላከል ይችላል፡፡ ጋዜጠኞች በጋራ ሥነ ምግባራዊ መርህ እንዲመሩ ሲያደርግ በዚያው ልክ የጋዜጠኞች መብት ያለአግባብ እንዳይጐዳ ይጠብቃል ማለት ነው፡፡ በመንግሥትና በሚዲያው ተዋናዮች መካከል የነበረው አለመተማመን እንዲሻሻል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡ በመንግሥት ሚዲያና በግል ሚዲያ መካከል ያለው ጽንፍ የወጣ አመለካከት ቀርቶ ሙያው ብቻ ማዕከል እንዲሆን ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብዬ አስባለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያው የሚዲያ ካውንስል መርሆ የሌሎች አገሮችን የሚዲያ ካውንስል ልምዶችን ያገናዘበ ነው ወይ?

ዶ/ር ነገሪ፡- የሚዲያ ካውንስል ጽንሰ ሐሳብ የመነጨው በቅርብ ዓመታት አይደለም፡፡ የቆየና ብዙ ጊዜ ያሳለፈና በርካታ ልምዶችን የያዘ ዓለም አቀፍ መርህ እየሆነ ነው የመጣው፡፡ ከአሜሪካ ጀምሮ ኃያላን አገሮች በዚህ መርህ ነው የሚመሩት፡፡ ኢትዮጵያ ወዳለችበት አካባቢ ስንመጣም ኬንያ፣ ታንዛኒያ፣ የኡጋንዳና የመሳሰሉት አገሮች ይህንን ካውንስል መሥርተው እየተጠቀሙበት ይገኛሉ፡፡ በአጠቃላይ በመመሥረት ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ሚዲያ ካውንስል ከሌሎቹ ጋር ስናነፃፅረው የተሻለ የሚባል ግምገማ ነው በእኔ በኩል ያለው፡፡ አንዱ የተሻለ ነው የምለው የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ ያስገባ ነው፡፡ የአገሪቱ ብዝኃነት ተቀብሎ እንዴት ነው መንከባከብ የሚገባኝ የሚለውን በአፅንኦት የተመለከተ ነው፡፡ ስለዚህ የሚመሠረተው የሚዲያ ካውንስል ጋዜጠኞችንም ሆነ የሚዲያ ተቋም ባለቤቶችን አንድ ወጥ በሆነ ለአገሪቱ ይጠቅማል ተብሎ በተዘረጋ ሥርዓት ውስጥ ለመንቀሳቀስ ያግባባ ነው፡፡ ሌላው ሁለቱንም የሚዲያ ዓይነቶች ማለትም የኤሌክትሮኒክና የሕትመት ሚዲያውን በአንድ ያቀፈ ነው፡፡

በአንዳንድ አገሮች የፕሬስ ካውንስል የሚል ስያሜ ይዘው የሚያስተናግዱት የሕትመት ሚዲያውን ብቻ ነበር፡፡ የኤሌክትሮኒክ ሚዲያው ደግሞ ሲስፋፋ ትልቅ ችግር የተፈጠረባቸው አሉ፡፡ ለምሳሌ የህንድን መመልከት ይቻላል፡፡ ፕሬስ ካውንስል ኦፍ ኢንዲያ ነበር የሚባለው፡፡ በሥሩም የሕትመት ሚዲያዎችን ነበር ያቀፈው፡፡ የህንድ መንግሥት ከ1990ዎቹ ጀምሮ የኤሌክትሮኒክ ሚዲያ እንዲስፋፋ ሲፈቅድና የውጭ ባለሀብቶችም በዚህ ዘርፍ እንዲሳተፉ ሲደረግ ቀድሞ የተመሠረተው የፕሬስ ካውንስል ሊያስተናግዳቸው ባለመቻሉ ችግር ተፈጥሮ ነበር፡፡ የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎች የራሳቸውን ካውንስል አቋቁመው እርስ በርስ ጠላትና ተፎካካሪ ነው የሆኑት፡፡ በመሆኑም ውጤታማ መሆንም አልቻለም፡፡

የኢትዮጵያ የሚዲያ ካውንስል ስያሜው የመገናኛ ብዙኃን ካውንስል ሆኖ ሁሉንም ማለትም የመንግሥትንም የግሉንም፣ ጋዜጣውንም ኤሌክትሮኒክ ሚዲያውንም ማቀፉ ችግሩን ቀድሞ የተገነዘበ ያደርገዋል፡፡ ዓላማውም የጋዜጠኝነት ሥነ ምግባር መርህን የሚጥሱ ጋዜጠኞችን እያደነ ጥፋተኛ ማድረግ ብቻ ሳይሆን፣ ከጋዜጠኞች ጎን የመቆምና አቅም የመገንባት ሥራንም ይሠራል፡፡ በአጭሩ አሁን ባየሁት ደረጃ የተሻለ ነው፡፡ ነገር ግን ባለድርሻ አካላት ከማቋቋም ባለፈ የባለቤትነት ስሜት ኖሯቸው በፍጥነት ወደ ሥራ መግባት የማይችሉ ከሆነ ፖሊሲ ሆኖ ብቻ ነው የሚቀረው፡፡ ዛሬ በከፍተኛ ፍላጐት የወደፊት የተሻለ የሚዲያ ተግባርን እየጠበቅን፣ ከተቋቋመ በኋላ መሥራት አልቻለም እንዳንባል እሰጋለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- በሚመሠረተው የሚዲያ ካውንስል ውስጥ መንግሥት አባል እንደሚሆን ተገልጿል፡፡ በዚህ የተነሳም የካውንስሉ ነፃነት ጥያቄ ውስጥ ወድቋል የሚል ክርክር ይደመጣል፡፡ በዚህ ላይ ምን ይላሉ?

ዶ/ር ነገሪ፡- በዚህ ላይ ማለት የምችለው መንግሥት የሚለውን ሐሳብ በድጋሚ መግለጽ ወይም ማብራራት ነው፡፡ መንግሥትን እንደምናውቃቸው የኢትዮጵያ መንግሥታት ብቻ የምንገልጸው ከሆነ ካውንስሉ ውስጥ መግባት የለበትም፡፡ መንግሥትን በዲሞክራሲ የሚያምንና በሕግ የበላይነት የሚገዛ ነው ብለን ትርጓሜ ከሰጠነው ግን የመንግሥት መግባት ምንም ችግር የለውም፡፡ መንግሥት እዚህ ካውንስል ውስጥ የሚንቀሳቀሰው እንደ አንድ አባል ነው፡፡ የሌሎችን እጅ የመጠምዘዝ አቅም አይኖረውም፡፡ መንግሥት በአባልነት የማይኖር ከሆነ ምን ዓይነት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል የሚለውን ጥያቄም መጠየቅ ይኖርብናል፡፡ የመንግሥት ድምፅ በማይኖርበት ወቅት መንግሥት ይህንን ካውንስል እንደ ጠላት ወይም እንደ ሥጋት አድርጐ ሊያየው ይችላል፡፡ ወይም የራሱን መቆጣጠሪያ ሥልት ሊያበጅ ይችላል፡፡ ያ ደግሞ ተያይዞ መውደቅ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ሚዲያ በሁለት ጽንፍ የቆመ መሆኑ ይታወቃል፡፡ እነዚህ ናቸው አንድ ላይ ተሰብስበው የሚዲያ ካውንስሉን ለመመሥረት ጫፍ የደረሱት፡፡ የተለያዩ ጽንፎችን የያዙ ተቋማትና ግለሰቦች በዚህ ካውንስል ውስጥ በመግባባት ምን ያህል ሊጓዙ ይችላሉ?

ዶ/ር ነገሪ፡- ቀደም ሲል በአንድ ጥላ ሥር የሚሰበስባቸው ተቋም ባለመኖሩ የየራሳቸውን ባህሪ ይዘው ተፃራሪ ሆነው ቆይተዋል፡፡ አሁን ግን ይህ ካውንስል የሚሠራው የጋዜጠኝነት ሙያ በባለሙያና በሙያው ሥነ ምግባር መሠራት አለበት በሚለው በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያለውን መርህ ለማስረፅ ነው፡፡ ይህንን የማይቀበል የሕዝብንም አመኔታ አያገኝም፡፡ በመሆኑም ከካውንስሉ ይወጣል፡፡ ከካውንስሉ ከወጣ ደግሞ የሚወድቀው የአገሪቱ የሕግ ማዕቀፍ ውስጥ ነውና የተሻለውን እንዲመርጥ ይገደዳል፡፡ በእኔ እምነት በሚዲያ ካውንስል ውስጥ ተግባብቶ መሥራት ካላስፈላጊ ክሶች ያድናል፣ የሙያውን ክህሎት ያዳብራል፡፡ ይህንን መገንዘብ የሚችሉ በመሆናቸው ተግባብተው ይሠራሉ ብዬ ነው የማምነው፡፡ እንዲያውም የሚደያ ካውንስል እንደ ወንፊት እንክርዳዱን ለመለየት የሚያስችል ሆኖ ያገለግላል፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ ካውንስል ተመሥርቶ ሥራ ቢጀምር በመጀመሪያዎቹ ዓመታት ምን ዓይነት ችግሮች ሊገጥሙት ይችላሉ ብሎ መገመት ይቻላል?

ዶ/ር ነገሪ፡- አንድ አዲስ አስተሳሰብ ሲመጣ ብዙ ችግሮች ሊያጋጥሙ ይችላሉ፡፡ አንደኛ የፋይናንስ ችግር ሊሆን ይችላል፡፡ ምክንያቱም ፋይናንስ ሊያደርጉ የሚችሉ ግለሰቦችም ሆነ ተቋማት ስለመጣው አስተሳሰብ እርግጠኛ መሆን ስለሚያቅታቸውና በሌሎችም ምክንያቶች ሊሆን ይችላል፡፡ ይህንን ለመቅረፍ የማስተዋወቅና ሐሳቡ በኅብረተሰቡ ዘንድ በጊዜ ተቀባይነት እንዲያገኝ ከተደረገ ፋይናንስ ችግር ይሆናል ብዬ አላምንም፡፡ ነገር ግን ትልቅ ችግር ይሆናል ብዬ የምገምተው ካውንስሉ በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት እንዳይኖረው የስም ማጥፋት ዘመቻ በማኅበራዊ ድረ ገጾች ይከፈትበታል የሚለው የራሴ የግሌ አስተሳሰብ ነው፡፡ በተለይ የዳያስፖራ ማኅበረሰቡ ከአገር ውስጥ የሚመነጩ ሐሳቦችን በተለይ ደግሞ መንግሥት የሚሳተፍበት ከሆነ በጭፍን የመጥላትና ዘመቻ የመክፈት ዝንባሌ አለው፡፡ ይህ በሚመሠረተው ካውንስል ላይ ኅብረተሰቡ እምነት እንዳይፈጥር ተፅዕኖ ሊያደርግ ይችላል፡፡ ይህንን ከወዲሁ ተገንዝቦ መቋቋም መቻል አለበት፡፡

የገንዘብ ችግር እንዳይፈጠር መንግሥት ከተለያዩ የአገር ውስጥ ምንጮች ማግኘት እንዲቻል መፍቀድ ይኖርበታል ብዬ አምናለሁ፡፡ አፍሪካ ውስጥ ያሉ ፍላጐት ያላቸው ተቋማት ካሉም ቢፈቀድ ጉዳት ይኖረዋል ብዬ አላስብም፡፡ ሌላው ተግዳሮት ይሆናል ብዬ የማስበው የዝግጁነት ጉዳይ ነው፡፡ እያንዳንዱ ባለድርሻ አካላት ሙሉ በሙሉ ዝግጁ መሆን አለበት፡፡ እኛ አገር እንደሚታወቀው አንድን አዲስ ሀሳብ ተግባራዊ ለማድረግ ጊዜ ይወስዳል፡፡ የሚዲያ ካውንስል አባላቱ በሐሳቡ ላይ በፍጥነት ተግባብተውና ተቀብለው ተቋሙን የራሳቸው አድርገው መቁጠር ላይ ሊዘገዩ ይችላሉ፡፡ ይህ እንዳይፈጠር ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ካውንስሉ የሚመጡለትን ሥራዎች በኃላፊነትና በፍጥነት መፍትሔ የማያበጁ ከሆነ፣ በመንግሥት ላይ ጥርጣሬን ሊያሳድሩና መንግሥት የራሱን መንገድ እንዲፈልግ ሊያስገድዱ ይችላሉ፡፡ ይህንን ከአሁኑ ሊፈጠሩ ይችላሉ ብሎ ገምቶ ችግሮቹን ከወዲሁ መቅረፍ ያስፈልጋል፡፡

Advertisements