አዲስ አበባ የማናት??


OromoFDG2014_Wallaggaa_1
ሰሞኑን በተለያዩ ዩንቨርሲቲ የሚማሩ የ”ኦሮሞ” ተማሪወች የአዲስ አበባ አስተዳደርና የኦሮሚያ ክልል ባለስልጣናት ሙያተኞችን አስተባብረው ባዘጋጁት የተቀናጀ ማስተር ፕላን አንፃር ስጋታቸውን ለመግለፅ አደባባይ ወጥተው አይተናል፡፡
ስጋታቸው በጥቅሉ “የኦሮሚያ መሬት ለአዲስ አበባ ሆነብን” የሚል ይመስላል ፡
እንዴት ነው ነገሩ?
አዲስ አበባ ታዲያ የማን ናት? ወይስ ኦሮሚያ የማናት? ኦሮሚያን ለ”ኦሮሞ” ሰወች የሰጠው ማነው? አማራንስ ለ”አማራ” ሰወች የሰጠው ማነው? ወይስ “ኦሮሞ” “አማራ” መባሉ በምንድን ነው? በቋንቋው? በሃይማኖቱ? ወይስ በደሙ? ነገር ግን ኦሮምኛ ወሎ ውስጥ አለ ፡ አማርኛም አርሲ ውስጥ አለ ፤ ዳግመኛም እስልምና ወሎ ውስጥ አለ ፡ ክርስትናም ወለጋ ውስጥ አለ ፤ ወይስ ስለደም ላውራ? ወሎየ ወይም ጎጃሜ ሆኖ ከቦረና ሰወች ጋር አልተጋባሁም አልተዋለድኩም ደም አልወረስኩም የሚል ማነው? ወይስ አርሲ ሆኖ ከጎራጌ ጋር ከወሎየው ጋር አልተጋባሁም ደም አልወረስኩም የሚል ማነው?
አንሳሳታ!!! የትግራዩአ ባድሜ በኤርትራውያን የተወረረች ጊዜ ታዲያ የወለጋው ወንድሜ ስለምን ደሙን አፈሰሰ? የጎጃሙ ወጣትስ ስለምን ነፍሱን ሰጠ? ባድሜማ የሽሬወች ብቻ ብትሆንና ለወለጋውና ለጎጃሜው ምንም ብትሆንማ ያ ሁሉ ህይወት ለምን መጥፋት አስፈለገው? ኢትዮጵያማ ሙሉዋን የትግሬ ካልሆነች ድርቡሾችን ስለመዋጋት ባልደከሙ ፤ መቀሌማ የኢሊባቦሩ ወጣት ካልሆነች እነፊታውራሪ ዲነግዴ እነባልቻ አባነፍሶ ጣልያንን ድል ስለማድረግ ሜዳ ተራራውን ፀሃይ ቁሩን ባላሳለፉ ፤
ጃገማ ኬሎን ጠይቁት ፡ በኢትዮጵያ መሬት ላይ ደሙን አፍስሷል ፡ ዘርአይ ደረስን ጠይቁት ስለኢትዮጵያ ባንዲራውን እንዳለበሰ ተሰውቷል ፡ አብዲሳ አጋን ጠይቁት ኢትዮጵያ የኢትዮጵያውያን እንጂ የአንደኛው ወይም የሌላኛው ብቻ እንዳይደለች ያስረዳችኅል፡፡ በላይ ዘለቀ የተዋጋው ለጎጃምና ለወሎ መሬት ወይስ ለኢትዮጵያ ነፃነት? ዋለልኝ የወደቀው ለጭቁኑ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ወይስ ለአንድ ዘር? ህውሃትንስ ምሬት ወልዶት መራራት ትግልን ያደረገው ለትግራይ ብቻ ወይስ ለኢትዮጵያ በሙሉ? ኢትዮጵያ ታዲያ የማን ናት?
እንግዲህ እኔን በየትኛው ክልል እንዳልኖር ትከለክሉኛላችሁ? አባቶቼ ካወረሱኝ ምድር ልታስወጡኝ እንዴት ይቻላችኅል? ትግራይ መኖር ብፈልግ የዮሃንስ ደም ለኢትዮጵያ ነፃነት ተገብሮባታልና ቦታ አለኝ ፡ ጎጃም ብሄድ በላይ ዘለቀ አለኝታየ ነው ፡ ጎንደር ብሄድ ቴወድሮስ አለኝታየ ነው ፡ ጅማ ብሄድ አባ ጅፋር በሩን ከፍቶ ያስገባኛል ፡ ሃረር ብሄድ ራስ መኮንንን አገኛለሁ ፡ ሽዋ ብፈልግ ምኒሊክን ባልቻን አያለሁ ፡ መላው ኦሮምያ ብዞርም እነ አብዲሳ አጋ እነጃገማ ኬሎ ምሳሌወቼ ናቸው ፡ ታዲያ ለኢትዮጵያ ደም አፍስሰው ለነፃነት ተዋድቀው ነፃ መሬት ያቆዩልን አባቶቻችን እያሉ እነ እንትና ተነስተው ይሄ የእኔ መሬት ነው ፡ ይሄኛው ላይ እንዳላይህ ሲሉ ራሳቸውን ፊውዳል እኔን ጭሰኛ ሊያደርጉ የሚተጉ እንዴት ያሉ አላዋቂወች ናቸው?
ወይንስ እስኪ ይሄን መልሱ ፦ ዛሬ ከምንበላው ከምንጠጣው እየቀነስን እያሰራነው ያለው የህዳሴ ግድብ የማን ነው? አስገራሚ ነው ፡ የኢትዮጵያ ወይስ የቤኒሻንጉል? ነገ ጥቂት የቤኒሻንጉል ሰወች ቢያኮርፉ ግድባችንን ልናጣ ነው? እስኪ ይህን መልሱ — እንዲህስ አይሁን ፡ ቤኒሻንጉል የእኛ ነው ፡ እኛም የቤኒሻንጉል ነን ፡ አማራ ያስተማረው ፡ ኦሮሞ ያስተማረው የለም ፡ አንዲት ኢትዮጵያ ሁላችንንም አስተምራናለች ፡ እኛም ለአንዲት ኢትዮጵያ ራሳችንን መስዋእት እናደርጋለን ፡ ይህን የቀደሙ አባቶች አውርሰውናልና፡፡
ታዲያ አዲስ አበባ የማን ናት? ——————- የሁሉም ኢትዮጵያዊ ናት፡፡
በተረፈ ግን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በእውቀትም ይሁን ያለእውቀት ሰላማዊ ሰልፍ በሚያደርጉበት ጊዜ በትእግስት በማስረዳት ጉዳዩ ላይ መስማማት ሲቻል አንድም በአስለቃሽ ጭስ ፡ በውሃ መበተን ሲቻል ያን ያህል ሰው መሞቱ ተገቢ አይደለምና የፀጥታ አስከባሪወች ጉዳዩን በጥበብ ትይዙት ዘንድ እመክራለሁ፡፡
ሰላም
Advertisements