ፖርቱጋላዊው ማርያኖ ባሬቶ የዋልያዎቹ አሰልጣኝ ሆነው ተመረጡ


barettoአዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 9 ፣ 2006 (ኤፍ.ቢ.ሲ.) የ57 ዓመቱ ፖርቱጋላዊው ማርያኖ ባሬቶ ዋልያዎቹን በዋና አሰልጣኝነት ለማሰልጠን ተመረጡ ።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በላከው መግለጫ ላይ እንዳመለከተው፥ ባሬቶ ከፊሊፖቪች እና ላርስ ኦሎፍ ጋር ተወዳድረዋል፡፡
ትላንት የመጨረሻ ዙሩ ንግግር ሲደረግ ዋናዎቹ ጉዳዮች የምክትል አሰልጣኝና የገንዘብ ጉዳይ የነበር ሲሆን ፥ሶስቱም አሰልጣኞች በገንዘቡ ተስማምተዋል ፤ ነገር ግን ፌዴሬሽኑ በነጥብ የተሻለ ሆነዉ ለነበሩት ባሬቶ አጽድቆላቸዋል፡፡
እናም በመጪዉ እሁድ አዲስ አበባ እንደሚገቡ የሚጠበቁት አሰልጣኙ ፥ ምክትል አሰልጣኝ በተመለከተ ከኢትዮጵያዊ አሰልጣኝ ጋር ተግባብቼ እሰራለሁ ማለታቸዉን አስታዉቀዋል፡፡
የትኛው አሰልጣኝ በሚለው ላይም ምርጫዉን እራሱ ባሬቶ ያደርጋል ተብሎ ነው የሚጠበቀው።
ስለዚህ በ15 ሺህ ዶላር ወርሀዊ ክፍያ ፖርቱጋላዊው ባሬቶ የዋልያዎች አሰልጣኝነት መንበር ተረክበዋል።
ፖርቱጋላዊው ማርያኖ ባሬቶ ከዚህ በፊት የጋናን ብሄራዊ ቡድን፣ የሩሲያውን ኩባን ክራስኖዳን እና ዳይናሞ ሞስኮ ክለብን እንዲሁም የዱባዩን አልናስር ክለብ በአሰልጣኝነት መርተዋል።
ዋልያዎቹን በዋና አሰልጣኝነት ለማሰልጠን ከተወዳደሩት 28 አሰልጣኞች መካከል አራቱ ተለይተው የቆዩ ሲሆን ፥ ማርያኖ ባሬቶ ባገኙት በአጠቃላይ ነጥብ ተመራጭ መሆናቸው ነው የተገለፀው።
Advertisements