የፈረንጆቹ አዲስ አመት አከባበርና ታሪክa_londre-aየአዲስ አመት በአል አከባበር ከሁሉም በአላት በቀደመ መልኩ እጅግ ጥንታዊነትን የተላበሰ ነው። በጥንታዊቷ ባቢሎን የዛሬዋ ኢራቅ የአዲሱ አመት ክብረ በአል ከአራት ሺህ አመት በፊት ይከበር እንደነበር የጽሁፍና የድንጋይ ላይ ስእል መረጃዎች ይጠቁማሉ። ባቢሎናውያን አዲሱን አመት ያከብሩ የነበረው ለአስራ አንድ ተከታታይ ቀናት ሲሆን በአሉን ተከትሎ ብዙ አስፈላጊ ክንውኖችም የሚካሄዱበት ወር ነበር አዲስ አመት።

የአዲስን አመት የማክበር በአል በሮማውያኖች ዘንድ የተጀመረው ደግሞ በ46ኛው አመተ አለም ሲሆን ወራቱም እንደዛሬው ጃኑዋሪ ወር ሳይሆን በማርች ወር መጨረሻ አካባቢ ነበር። በወቅቱ የነበረው የሮማ ገዢ ጁሊየስ ቄሳር ወራቱን ከማርች ወደ ጃንዋሪ 1 ቀን በመቀየር እንዲከበር አደረገ። የጃንዋሪ ወር ስም አሰጣጥም ከሮማውያኖቹ ጃኑስ አምላክ ስያሜ የተገኘ ሲሆን ትርጉሙም በሁለት አቅጣጫ የሚያይ ፊት ማለት ነው፡፤ አንዱ ፊት ለፊት ሲመለከት ሌላኛው የኋልዮሽ ይመለከታል። ጁልየስ ቄሳር ይህንን የጃንዋሪ ወር ምልክት የመረጠው ለበአሉ ትክክለኛ ትርጉም የሚሰጥ በማለት ነበር። ቄሳር ይህንን ብቻ ሳይሆን ከሱ በፊት የቀደሙት ነገስታቶች በአሉን በማርች ወር ያከብሩት ስለነበር አዲሱን አመት ክብረ በአል ወደ ጃንዋሪ ለማድረግ የአመቱን ቀናቶች በመግፋት አንዱን አመት ለ445 ቀኖች መጠበቅ ግድ ሆኖበት ነበር።

በመካከለኛው ክፍለ ዘመን የነበሩት አውሮፓውያኖች ካቶሊኮች ደግሞ የቄሳርን የጃንዋሪ ወር አዲስ አመት አከባበር የሃይማኖት የለሾች አከባበር በመሆኑ በአሉ ወደ ቀድሞው ወር መመለስ አለበት በማለት በ547 የቶርስ ጉባኤ ታሪካዊ ስብሰባ ላይ የአዲሱ አመት አከባበር እንደጥንታዊው የባቢሎናውያን አከባበር ማርች ወር ላይ እንዲሆን በመስማማት አጸደቁት።

በ1582 የግሪጎሪያውያን የቀን አቆጣጠር በስራ ላይ በመዋሉ የአዲሱ አመት አከባበር አሁንም እንደገና ወደ ጃንዋሪ 1 ቀን የመለወጥ እድል አገኘ፡፤ ይህንንም ቀን በአውሮፓ የሚኖሩና እንዲሁም የግሪጎሪያውያንን የዘመን አቆጣጠር የሚከተሉ ሃገሮች ለውጡን ተግባራዊ ሲያደርጉት የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች ግን ለውጡን አንቀበልም በማለት በቀድሞው እለት በአሉን ማክበር ጀመሩ። እንግሊዝና የአሜሪካን ቅኝ ተገዢዎቻቸውም አዲሱን የበአል አከባበር ሳይቀበሉ እስከ 1752 ድረስ ዘልቀዋል።

የአዲስ አመት አከባበር ስርአቶች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ከጥንታዊያኖች የአከባበር ባህሎች ጋር እጅግ የተቀራረበ ቁርኝት አላቸው፡፡ የአዲስ አመት ትውፊት በጥንታውያን ግሪኮች ቅርጻ ቅርጾችና የድንጋይ ላይ ጽሁፎች ተቀርጸው ተገኝተዋል። በአዲስ አመት አዲስ ተስፋን ሰንቆ በአዲስ መንፈስ አመቱን መጀመር በአብዛኛው የአለማችን ክፍል ተመሳሳይነት ቢኖረውም በአሉን በማስመልከት የሚደረገው የአከባበር ስነ ስርአት ግን ከሃገር ሃገር የተለያየ ነው፡፤
• እስራኤላውያን ምንም እንኩዋን የግሪጎሪያውያንን የቀን አቆጣጣር ቢከተሉም በአሉን ግን ይፋ በሆነ መንገድ አያከብሩትም፤ የሚሰጡትም ምክንያት ከሚከተሉት የይሁዲ( ጂዊሽ) እምነት ጋር ተጻራሪ ነው የሚል ነው። በአንጻሩ ቁጥራቸው ጥቂት የማይባሉ እስራኤላውያን በአሉን በተለያዩ ዝግጅቶች በማድመቅ Rosh Hashanah በተባለው ስፍራ ያከብሩታል። በእስራኤል የሚኖሩ የእስልምና እምነት ተከታዮች የሉናር የቀን አቆጣጠርን ስለሚከተሉ አዲሱን አመት በየአመቱ በተለያዩ ቀናቶች ያከብሩታል።
• ህንዳውያን ደግሞ አዲሱን አመት በቀን መቁጠሪያቸው መሰረት ጸሃይ ወደ ሜሻ በጠለቀች ጊዜ( ጃንዋሪ 1 ቀን ማለት ነው) በአሉን ያከብሩታል። በአዲሱ አመትም ህንዳውያን ለቤተሰቦቻቸውና ለአረጋውያን ያላቸውን ክብር ሲገልጹ አነስተኛ የሆነች ከነሃስ የተሰራች ቶክን( ሳንቲም) በመሰጣጣት አዲሱ አመት የደስታና የብልጽግና እንዲሆንላቸው ምኞታቸውን ይለዋወጣሉ
• ጃፓናውያኑም እንደዚሁ አዲሱን አመት በደስታና በጭፈራ የሚያሳልፉበት ወቅት ነው። ጃፓናውያን የቻይናን የቀን አቆጣጠር በመተው የጎርጎሪሳውያንን አቆጣጠር ማክበር ከጀመሩ ሰነባብተዋል።
• አዲሱ አመት በቻይናና በተለያዩ የሉናር የቀን አቆጣጠር በሚከተሉት ሀገራት እንደ ኮሪያ፤ ቪየትናም እና በአብዛኛው የእስያ ሀገራት በአሉ በተለያዩ ጣእመ ምግቦች፤ በጭፈራና እንዲሁም ቀይ ፖስታ በመለዋወጥ እና አካባቢውን በመልካም እድል ተምሳሌት ቀይ ቀለም በማስጌጥ ያከብሩታል( ቀዩ ፓስታ ብዙውን ጊዜ ገንዘብ በውስጡ ይደረግበታል) የአዲስ አመት አከባበር በብዙ የርችት ተኩሶችና ብዙ አዝናኝ ትርኢቶች የተሞላ በመሆኑ በአብዛኛው ቻይናውያን በተለይም በወጣቶች ዘንድ እጅግ የሚናፈቅ ክብረ በአል ነው።
• በቀድሞዋ የሶቪየት ግዛቶችና በሩሲያ እለቱ የሚከበረው ርችቶችን በመተኮስና የቮድካ መጠጥን በመጎንጨት አሮጌውን አመት በመሰናበት አዲሱን አመት ይቀበሉታል
• በአሜሪካን ግዛት ኒውዮርክ ደግሞ የአዲሱ አመት አከባበር ፍጹም የተለየና ደማቅ ነው። 11.875 ፓውንድ ክብደት ያለው ኩዋስ ከከፍተኛ የብረት ማማ ላይ በማንጠልጠል አሮጌው አመት ሊጠናቀቅ አንድ ደቂቃ ብቻ ሲቀረው በየአንዳንዱ ሴኮንድ ዝቅ እያለ መውረድ ይጀምራል፡፡ ልክ ከምሽቱ አስራ ሁለት ሰአት( 12 ኤ.ኤም) ላይ ሲሆንም የአዲሱ አመት መግባት ማብሰሪያ የሆነው ርችት መተኮስ ይጀምራል። ርችቱንም ተከትሎ በተለያዩ ታዋቂ አርቲስቶች የሚቀርቡ የሙዚቃ ዝግጅቶችም የኒውዮርክን ነዋሪ ብቻ ሳይሆን ይህንን ትርኢት ለመመልከት ከአለም ዙሪያ ለተሰባሰቡ ጎብኚዎችም አስደሳች የጊዜ ማሳለፊያ ነው የአዲስ አመት ዝግጅት።
• በተለያዩ ሃገራት በተለይም ቀዝቃዛ የአየር ንብረት ባላቸው ሃገሮች በአሉን በበረዶ በተሸፈኑ ወንዞች ውስጥ በመነከርና በወንዙ ዙሪያ በፍጥነት በመሮጥ ጥንካሬያቸውን በማሳየት ሲያከብሩት በአንዳንድ ሀገሮች ደግሞ እለቱን የእርዳታና የበጎ አድራጎት ገንዘብ መሰብሰቢያ ቀን በማድረግም ያሳልፉታል። እኛ ኢትዮጵያውያን ደግሞ የራሳችን የዘመን አቆጣጠር ስላለን አዲሱን አመት ከሚያከብሩት ጋር ተመሳስለን ከማክበር ውጪ ብዙም የምናደርገው ነገር አይኖርም፡፡ነገር ግን በሮም ውስጥ ስትኖር ሮማውያኖችን ምሰል እንደሚባለው ግን በአሉን በተወሰነ መጠን ብናከብረውም ደስታን ከመጨመር ውጪ የሚጎዳን ነገር የለውም።
• በአዲሱ አመት የመጀመሪያ ደቂቃዎች የሚወለዱ ህጻናት የአዲስ አመት በረከቶች በመባል ይታወቃሉ። በተለይ ባለንበት አሜሪካ ለእንደዚህ አይነት ውልደቶች ሽልማቶችና ስጦታዎች ይሰጣሉ። ምናልባትም ፕሮግራማችንን የምትከታተሉ አድማጮቻችን በሚቀጥለው አመት መግቢያ ደቂቃ ላይ የልጅ በረከት ካገኛችሁ የሽልማት እድለኞች መሆናችሁንም ልናስታውሳችሁ እንወዳለን።

እንግዲህ በማጠቃለያችን የአዲስ አመት አከባበርና እለቱ ከጥንት ጀምሮ በብዙ ለውጦች ውስጥ ማለፉን እንረዳለን፡፤ በዘመናት ሂደት ግን አንድ ያልተለወጠ ሃቅ አለ፤ ይሄውም በአዲስ አመት በመላው አለም የሚኖሩ ህዝቦች የነገን አዲስ ህይወታቸውን በአዲስ ተስፋ ሰንቀው ለአዲስ ጉዞ አንድ ብለው የሚጀምሩበት ቀን ነው አዲስ አመት፡፤ እንግዲህ በአዲሱ የፈረንጆች አመት የተጣላችሁ ታርቃችሁ፤ የተነፋፈቃችሁ ተገናኝታችሁ፤ ፍቅረኛ ያጣችሁ አግኝታችሁ፣ ትጭጭት ያደረጋችሁ ተጋብታችሁ፤ የተጋባችሁ ወልዳችሁ፤ ስራ ያጣችሁ ስራ አግኝታቹህ፤ ጤና ያጣችሁ ጤና አግኝታችሁ፤ የታሰራችሁ ተፈታችሁ፤ ለማየት ያብቃን እያልን እንሰናበታለን። መልካም የፈረንጆች አዲስ አመት!

(Source Admas Radio Atlanta)