አዲሲቷ ደቡብ ሱዳን በአሮጌው ሕመም


df87ed4049c5c922a3d49a57e984f444_Lቴልሳች ጋድ በዓረብኛ ቋንቋ አስተማሪነት የሠለጠነ ወጣት ነው፡፡ በደቡብ ሱዳን ዋና ከተማ ጁባ የነበሩ ሁለት የሮይተርስ ጋዜጠኞች በአንዱ ጎዳና ላይ ከሚገኙ ካፌዎች መካከል ከሌሎች ወጣቶች ጋር ቁጭ ብሎ አግኝተውታል፡፡ ወጣቶቹ ሥራ አጦች ናቸው፡፡ ፊታቸው ላይ ደስ የማይል ነገር ይነበባል፤ ቀቢፀ ተስፋ፡፡

ጊዜው ባለፈው መስከረም ወር ነው፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት ከሰሜንዋ ሱዳን በሪፈረንደም የተለየችው አዲሲቷ አገር ቴልሳች የተሻለ ሕይወት ለመምራት ተስፋ ሰንቆባት ነበር፡፡ ዳሩ ግን አልሆነም፡፡ ‹‹መንግሥት ምንም ተስፋ የሚሰጥ ነገር እየሠራ አይደለም፤ ሥራ የለንም፡፡ ትምህርት ቤት የለም፡፡ ሆስፒታል የለም፤›› ይላል ተስፋ በመቁረጥ መንፈስ፡፡

ሰሞኑን በአገሪቱ በተደረገው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ከአንድ ሺሕ በላይ ሰዎች መሞታቸው ተሰምቷል፡፡ በፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪርና ቀደም ሲል ከሥልጣናቸው ባበረሩዋቸው ምክትላቸው ሪክ ማቻር ደጋፊዎች መካከል የእርስ በርስ ግጭት ቀጥሏል፡፡ ግጭቱ የጎሳ ገጽታ እየያዘ በመሆኑ፣ የአገሪቱ መከላከያ ኃይልም በሁለት ተከፍሏል፡፡ ሁለቱም መሪዎች ለመደራደር የሚያደርጉት ሙከራም እስካሁን ፍሬ አላፈራም፡፡

ያላጣጣሙት ነፃነት

ካርቱም በሚገኘው የሱዳን መንግሥት ዘርፈ ብዙ ብሔራዊ ጭቆና የደረሰባቸው ደቡብ ሱዳኖች ራሳቸውን ነፃ ለማውጣት ከ20 ዓመታት በላይ ታግለዋል፡፡ ውዝግቡ ከሁለት ዓመት በፊት በሕዝብ ውሳኔ ከመጠናቀቁ በፊት፣ የእርስ በርስ ጦርነቱ ከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ መስዋዕትነት ተከፍሎበታል፡፡ በአፍሪካ ዝናቸው የናኘው የነፃነት ታጋዩ ዶ/ር ጆን ጋራንግ ሳይቀሩ የብዙ ሰዎች ሕይወት ጠፍቷል፡፡ በሁለቱም ወገን ለሞት የተዳረጉት፣ የተፈናቀሉትና ለስደት የተዳረጉት ቁጥር ስፍር የላቸውም፡፡

የአፍሪካ ኅብረት የሚመራው ሁለገብ የሰላም ስምምነት (CPA) መሠረት የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው የወሰኑት ደቡብ ሱዳናውያን ራሳቸውን ከሰሜኖቹ ጭቆና ነፃ ለመውጣት 98 በመቶ ድምፃቸውን ለመገንጠል ሰጥተው ነበር፡፡ ነፃነታቸውን በቀላሉ ይሰጣል ተብሎ ያልተገመተው የፕሬዚዳንት አል በሽር መንግሥት፣ ከውጭም ከውስጥም በደረሰበት ጫና ምክንያት ውሳኔውን ለመቀበል አላቅማማም ነበር፡፡

ያም ሆኖ በኢትዮጵያና በኤርትራ መለያየት ጊዜ የተፈጠረው የድንበርና የሀብት ክፍፍል ዓይነት ችግሮች በይደር ነበር የቆዩት፡፡ በመሆኑም አዲሲቷ ደቡብ ሱዳን ገና በሁለት እግሯ ሳትቆም ከእናት አገሯ ጋር ወደ ጦርነት መግባቷ አልቀረም ነበር፡፡ የሁለቱን አገሮች ውዝግብ ለመፍታት ጥረት እየተደረገ በመሆኑ በኢትዮጵያና በኢጋድ ሸምጋይነት የሰላም ሒደቱ በትግበራ ላይ ይገኛል፡፡ ከፖለቲካ ሽምግልናው ባሻገር ግን ደቡብ ሱዳናውያን ፍዳቸውን እያዩ ነው፡፡ በሁለቱም ወገኖች ፍላጎት በአወዛጋቢዋ በዓቢዬ ግዛት የኢትዮጵያ ወታደሮች በተመድ ሥር በሰላም ማስከበር ሥራ ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ፡፡

በቀውሱ ዋዜማ

ደቡብ ሱዳን ነፃ የወጡት ዜጎቿ እንደገመቱት ሕይወት አልጋ በአልጋ ሊሆንላቸው አልቻለም፡፡ በነዳጅ ሀብቷ የምትታወቀው ደቡብ ሱዳን ከምዕራባውያን አገሮች በብዙ ቢሊዮን የሚቆጠሩ ዶላሮች ዕርዳታ ማግኘቷን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ዜጎች ግን እንዳሰቡት ሕይወታቸው አልተሻሻለም፡፡ ሥራ አጥነት ተስፋፍቷል፣ ወንጀል ተበራክቷል፣ ሙስና በከፍተኛ ደረጃ ተንሰራፍቷል፣ ፍትሕና መልካም አስተዳደር ብሎ ነገር የለም፡፡ ለዚህም ዋናው ምክንያት በሳልቫ ኪር የሚመራው መንግሥት የአገሪቱን ኢኮኖሚ እንደታሰበው ሊያሳድገው ባለመቻሉ ነው፡፡ በመሆኑም ሮይተርስ ቴልሳች ጋድን ባነጋገረበት ሳምንት በደቡብ ሱዳን ጎዳናዎች ላይ መጠነኛ የሆነ የወጣቶች አመፅ ተከስቶ ነበር፡፡

ኢንተርናሽናል ሪፐብሊካን ኢንስቲትዩት የተባለው ተቋም ከአካባቢው በሰበሰበው የሕዝብ ድምፅ፣ በአገሪቱ 50 በመቶ ሕዝብ ደቡብ ሱዳን በተሳሳተ አቅጣጫ እየተጓዘች ነች ብሎ ያምናል፡፡ የደቡብ ሱዳን የሲቪል ማኅበረሰቦች ትብብር ኃላፊ የሆኑት ዳንግ አቱይ፣ ‹‹ሕዝቡ ስለሚበሳጭ አንድም ደስተኛ ሰው አታገኝም፤›› ማለቱን ሮይተርስ በዘገባው አስፍሯል፡፡

‹‹ሕዝቡ ውስጥ ፍርኃት ነግሷል›› የሚለው ደግሞ ሴሰር አጃ የተባሉ የፕሮቴስታንት ፓስተር ናቸው፡፡ በሥራ አጥነትና በድህነት ምክንያት ሰዎች ራሳቸውን እያጠፉ መሆናቸው የገለጹት እኚህ ይኸው ፓስተር፣ በቤተ ክርስቲያናት የምክር አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸው ተናግረዋል፡፡ ሕዝቡ ፍርኃት ውስጥ በመግባቱ ወደ ጎዳና አመፅ ከመውጣት ይልቅ ወደ እምነት ቦታዎች በመምጣት ምሬቱን እያሰማ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡

የተወላገደችው ደቡብ ሱዳን

ሁለቱ አገሮች ከመለያየታቸው በኋላ በይደር የቀሩት ጉዳዮች ወዳልተፈለገ ቀውስ ያመሩዋቸዋል የሚሉ መላምቶች ይሰሙ ነበር፡፡ ይህ ሥጋት የብዙኃኑ የፖለቲካ ተንታኞች ሥጋት ቢሆንም፣ ጥቂት የማይባሉትም አዲሲቷ ደቡብ ሱዳን ያልተገመቱ የፖለቲካ ችግሮች ሊገጥሟት እንደሚችሉ ያስጠነቅቁም ነበር፡፡ የሥርዓቱ አወቃቀር፣ የብሔር ክፍፍል፣ ሥራ አጥነት፣ ድህነትና ሙስና የውስጥ ሥጋቶች መሆናቸውን ገልጸው ነበር፡፡

ደቡብ ሱዳን በሕዝበ ውሳኔ ነፃ መውጣቷ በታወጀ ማግስት የኦስካር አሸናፊው የፊልም ባለሙያ ጃሚ ዶራን የሠራው ዶክመንተሪ ፊልም በአልጄዚራ የተሠራጨው በሦስት ክፍሎች ነበር፡፡ ፊልሙ የመጀመርያው የትግል አካል መጠናቀቁን፣ ዋናውና የአገር ግንባታ ፈተና ግን ደቡብ ሱዳን የምትጋፈጠው የውስጥ ችግር ገና መሆኑን የሚያሳይ ነበር፡፡

በፊልሙ በተላለፈው ገዢ ሐሳብ በፀረ ሰሜን የተደረገው ትግል አጓጊ ያደረገው በደቡብ ሱዳን የሚገኙ የተለያዩ ጎሳ አባላት የጋራ ጠላት አንድ አድርጓቸው ቢቆይም፣ ከዚያ በኋላ እንዴት አብረው መኖር እንዳለባቸው አላሰቡበትም የሚለው የጎላ ነበር፡፡

ለሩቅ ተመልካች አንድ አገር መስላ የምትታየው ደቡብ ሱዳን፣ በውስጧ ምንም አንድነት እንደሌለና በዚህ መሀል በመሪዎች መካከል ሊፈጠር የሚችለው ሙስና የአገሪቱን አንድነት የሚፈታተኑ ተግዳሮቶችን የሚያሳይ ነበር፡፡

በወቅቱ የጋራ ጠላት አንድ ያደረጋቸው መሪዎች በቀጣይነት በመካከላቸው ሊከሰት ስለሚችለው መለያየት ምንም ትኩረት ያልተሰጠው ሕመም እንደሆነ በፊልሙ ተገልጾ ነበር፡፡ ችግሩ በጊዜ ካልተፈታ ብዙም ሳይቆይ አንድ ቀን እንደሚፈነዳ ፊልሙ ሠሪው አስጠንቅቆ ነበር፡፡ አሁን ደቡብ ሱዳን ውስጥ የሆነው ከሁለት ዓመት በፊት በዚህ ፊልም የተነገረው ትንበያ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡

በተለይ ደግሞ በዚሁ ዘጋቢ ፊልም አስደናቂ ንግግር ካደረጉት አንዱ የአገሪቱ ባለሥልጣን ነበሩ፡፡ የአገሪቱ የባህል ሚኒስትር ዴኤታ የሆኑት ጃክ ማዶት፣ ‹‹አገሬ አራት እግር ያላት እንሰሳ ትመስለኛለች፡፡ እነዚህ እግሮች ግን ሁሉም የተጎዱ ናቸው፤›› ብለው ነበር፡፡

በእግር የተመሰሉት እነዚህ አገራዊ ጉዳዮች መከላከያ ኃይሉ፣ ሲቪል ማኅረሰቡ፣ አገልግሎት ሰጪው ቢሮክራሲና ፖለቲካ ናቸው፡፡ ‹‹በአራት የተጎዱ እግሮች እንደቆመች እንስሳ›› ያሏት ደቡብ ሱዳን ቀጣይ ዕጣ ፈንታ አጣብቂኝ ውስጥ እንደሆነ አብራርተው ነበር፡፡ ‹‹ዛሬ ይቺ እንስሳ በተጎዱ እግሮቿ ቆማለች፡፡ እነዚህ እግሮች በጊዜ ካልታከሙ የወደፊት ዕጣዋ ጨለማ ነው፤›› በማለት፡፡ የዚህ አባባል እውነታነት የተረጋገጠው ሰሞኑን በአገሪቱ ያጋጠመው ቀውስ ነው፡፡ ቀደም ሲል በአገሪቱ እየተስፋፉ በመጡ ችግሮች ምክንያት ግራ ተጋብተው ባለፈው ሐምሌ ወር ካቢኔያቸውን የበተኑት ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር፣ ምክትላቸው የነበሩትን ሪክ ማቻር ከሥልጣናቸው ማባረራቸው አሁን ለተከሰተው የመፈንቅለ መንግሥት መከራና ጎሳ የለየ ብጥብጥ ምክንያት መሆኑንና የእርስ በርስ ጦርነት መነሻ ተደርጎ እየተወሰደ ነው፡፡

ብዙዎች የአገሪቱ ዜጎች ሳልቫ ኪር ያለ ሪክ ማቻር ደቡብ ሱዳንን በሰላም መምራት አይቻላቸውም የሚል እምነት እንደነበራቸው አልጄዚራ ዘግቧል፡፡ ሁለቱም መሪዎች የአገሪቱን የትጥቅ ትግል የመራው የደቡብ ሱዳን ነፃ አውጪ ግንባር ከፍተኛ አመራሮችና ታጋዮች ናቸው፡፡ ከአንድ ወር በፊት ግን ቀደም ብሎ ሳልቫ ኪርን በአምባገነንነት በፈረጁት ሪክ ማቻር፣ በገዢው ፓርቲ ውስጥ ከፍተኛ መከፋፈል ለመፈጠሩ ማሳያ ሆኗል፡፡ ይህ መከፋፈል የጎሳ ጦርነት እያስጀመረ መሆኑም በስፋት ይነገራል፡፡

በፓርቲው ውስጥ የተከሰተው መሰንጠቅ ወደ መከላከያ ኃይሉ ዘልቆ የገባ ሲሆን፣ በሁለቱም መሪዎች ጎሳዎች መልክ መያዙም እየተነገረ ነው፡፡ ሳልቫ ኪር የዲንካ ጎሳ ተወላጅ ሲሆኑ፣ ማቻር ደግሞ የኑዌር ተወላጅ ናቸው፡፡ ቀደም ሲል በፓርቲው የፀደቀው ሕገ መንግሥት ለፕሬዚዳንቱ የሚሰጠው ሥልጣን የልተመጣጠነ መሆኑን በምክትል ፕሬዚዳንቱ ሲተች የነበረ ሲሆን፣ ሕገ መንግሥቱ የአገሪቱን ክልሎች ገዢዎች ሹም ሽረትን ጨምሮ፣ ካቢኔ የማቋቋምና የመሻር ሥልጣንም ይሰጣቸዋል፡፡ ከፖለቲካ ጀምሮ እስከ መከላከያ ኃይሉ ይህንን ሥልጣናቸውን አላግባብ እየተጠቀሙ ነው የሚል ስሞታ በምክትላቸው ሲቀርብባቸው የቆየው ሳልቫ ኪር፣ በተለይ ባለፈው ዓመት ከአንድ መቶ በላይ ወታደራዊ መኰንኖች በጡረታ እንዲገለሉ በማድረጋቸው ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሟቸው ነበር፡፡

ደቡብ ሱዳን በነዳጅ ሀብታቸው ከታወቁ የአፍሪካ አገሮች መካከል ግንባር ቀደም ስትሆን፣ ከሰሜኑ ሱዳን ባደረገችው ውል መሠረት እ.ኤ.አ. ከ2005 ጀምሮ እስካሁን አሥር ቢሊዮን ዶላር ማግኘቷን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ከዚህ ውስጥ ግማሹ በአገሪቱ ባለሥልጣናት መዘረፉ ሲነገር፣ ሳልቫ ኪር 75 የሚሆኑ ባለሥልጣናት የዘረፉትን ገንዘብ እንዲመልሱ ባለፈው ዓመት ያዘዙ ቢሆንም፣ እንዳልተሳካ ሮይተርስ ያነጋገራቸው አንድ ዲፕሎማት ተናግረዋል፡፡

በደቡብ ሱዳን ያለው ሙስና እጅግ የተጋነነ መሆኑን አንዳንድ ሪፖርቶች ያመለክታሉ፡፡ በተለይ በፖሊስ ውስጥ የተሠራው ምርመራ እንደሚያሳየው፣ አሥራ አንድ ሺሕ የሚሆኑ የውሸት ስሞች በደመወዝ መክፈያ ዝርዝር ውስጥ የተገኙ ሲሆን፣ ሌሎች አሥራ ስድስት ሺሕ ስሞችም በጥርጣሬ ይታያሉ፡፡

የሰላም ጥረቶች

በሳልቫ ኪርና በማቻር ደጋፊዎች መካከል የተጀመረው የእርስ በርስ ውጊያ እየተባባሰ ሲሆን ተመድ፣ አፍሪካ ኅብረትና የኢጋድ መሪዎች ባለጉዳዮቹ ለቀውሱ መፍትሔ ለማፈላለግ ችግራቸውን በጠረጴዛ ዙሪያ እንዲጨርሱ ጥሪ አድርገዋል፡፡ ከፍተኛ ጥረትም እያደረጉ ይገኛሉ፡፡

ባኒቱ የተባለችውን የዩኒቲ ግዛት ዋና ከተማ መቆጣጠሪያቸውን ያሳወቁት የማቻር ደጋፊ ጄነራሎች፣ ወደ ሌሎች አካባቢዎች እየገሰገሱ መሆናቸው ከፍተኛ ሥጋት ፈጥሯል፡፡ ዩኒቲ ግዛት የአገሪቱ 95 በመቶ የነዳጅ ምንጭ መሆኑ ደግሞ ሥጋቱን ከፍ አድርጎታል፡፡

አሜሪካን ጨምሮ የተለያዩ አገሮች ዜጎቻቸውን እያስወጡ ሲሆን፣ አንድ መፍትሔ ላይ ካልተደረሰ አገሪቱ ማለቂያ ወደ ሌላው እልቂት እንዳትገባ ተፈርቷል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና የኢጋድ ሊቀመንበር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ሁለቱን ወገኖች ለማደራደር በጁባ ከተማ ሰንብተዋል፡፡ ሁለቱም መሪዎች ለመደራደር ፈቃደኛ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ሆኖም እስካሁን ፊት ለፊት አቀራርቦ ማነጋገር አልተቻለም፡፡ መሪዎች በየፊናቸው ለመደራደር ፈቃደኛ መሆናቸው ቢገለፁም፣ በተለይ ማቻር ከመፈንቅለ መንግሥቱ ሙከራ በተያያዘ ተጠርጥረው የታሠሩት እንዲፈቱ በቅድመ ሁኔታ ማስቀመጣቸው ነገሩን ሳያካብደው አልቀረም፡፡ በቁጥጥር የዋሉት ባለሥልጣናትና ወታደራዊ ሹማምንት ተፈተው እንደ ኢትዮጵያ ወደ መሳሰሉ ገለልተኛ አገሮች ተላልፈው እንደሰጡ መጠየቃቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

በደቡብ ሱዳን አሁን የተከሰተው ቀውስ በጊዜ መፈታት ካልተቻለ በአጠቃላይ በአካባቢው ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ሊያሳድር እንደሚቻል የፖለቲካ ተንታኞች ያስረዳሉ፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ከደቡብ ሱዳን ጋር ቅርበት እንዳለው የሚገልጹት እነዚህ ተንታኞች፣ አሁን ሁለቱንም መሪዎች አቀራርቦ ለማደራደር በሁለቱም ወገኖች ዘንድ እንደ እውነተኛ ገለልተኛ ሆኖ ይታያል ይላሉ፡፡

ethiopianreporter.com

Advertisements