የአቦይ ስብሀት ነገር!


84437941c6b4017076c89a9feb5e93f2_XLከአሁን በፊት በዚሁ ርዕስ ፅሁፍ እንደፃፍኩ አስታውሳለሁ። አጋጣሚ ሆኖ ዛሬም ይህን ፅሁፍ ለመፃፍ በምነሳበት ወቅት ከዚሁ ርዕስ ሌላ ሀሳቤን በአንድነት ጭምቅ አድርጎ ሊገልፅልኝ የሚችል ርዕስ ሊመጣልኝ ስላልቻለ እንደገና በዚሁ ርዕስ መጠቀሙን ወደድኩ።

አባይ ስብሀት በልበወለድ ዓለም የተፈጠሩ ሰው ቢሆኑ ኖሮ እጅግ በጣም አጨቃቃጪ፣ አነጋጋሪና የተለየ ስብዕና ያላቸው ገፀ ባህርይ ሆነው የተቀረፁ እጅግ በጣም የተዋጣለት ገፀ ባህርይ ይሆኑ ነበር። የሚገርመው ነገር በእውኑ ዓለም ያሉ ሰው ሆኖው ሳለ እንዲህ ዐይነት አነጋጋረና ግራ አጋቢ የሆነ ገፀ ባህርይ ያላችው ሰው መሆናቸው ነው። ለዚህ ሳይሆን አይቀርም ብዙውን ጊዜ በሚናገሩት ነገር ሁሉ ትኩረት ሳቢ ሆነው የምናገኛቸው። ለዛሬ ባለፈው በህዳር 17 ቀን 2006 ዓ.ም. በአዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ዲፓርትመንት ተጋብዘው ተናገሩት ላይ ይሆናል ትኩረት የማደርግው። አቦይ ስብሀት በዩኒርሰቲው ተገኝተው ፖለቲካዊ ሀሳባቸውን ለተማሪዎች እንደሚያካፍሉ ዜናውን እንደሰማሁ ደግሞ ምን ሊሉ ይሆን ብዬ ነበር ከተወሰኑ ጓደኞቼ ጋር በመሆን እዚያ የተገኘሁት። እኔም የዩኒቨርሲቲው ተማሪ መሆኔ ጠቀመኝና የተማሪነት መታወቂያን አሳይቼ ወደ አዳራሹ ዘለኩ። አቦይ ስብሀት ሙሉ ለሙሉ ጥቁር የሆነ ሱፍ ለብሰው፣ ከፊት ለፊት በተደረደሩ መደዳ ወንበሮች ላይ ተሰይመዋል። ከዚያ ድፎ ዳቦ እንዲቆርሱ ተደረገና ወደ ዝግጅቱ፣ ዋናው ጉዳይ ተገባ። በአንድ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ዲፓርትመንት ተማሪ ጥያቄ አቅራቢነት አቦይ ስብሀት ለጥያቄዎቹ ሰፋ ያለ መልስ መስጠት ጀመሩ። ለዛሬ ትኩረቴን እጅግ ከሳቡኝና ግርምት ከፈጠሩብኝ የአቦይ ስብሀት ንግግሮች የተወሰኑትን እዚህ ላይ እያነሳሁ ሀሳብ እሰጥባቸዋለሁ።

1. ሀገር ማለት
አቦይ ስብሀት «ሀገር ማለት ህገ መንግስቱ ነው፤ ሌላ ነገር አይደለም።» የሚል ነገር ተናግሯል። ይሄ ለእኔ ምን ማለት እንደሆነ ግለፀው ብባል፤ እንዲህ በሌላ ምሳሌ ላስቀምጠው እችላለሁ። ትዳር ምንድነው ለሚለው ጥያቄ «ትዳር ማለት የጋብቻ ሰርቴፍኬት ማለት ነው።» ብሎ የመመለስ ያህል ነው። ይሄ አነጋገር ስሜት ሊሰጥ ይችላል?! ትዳርን ትዳር የሚያድርገው የጋብቻ ሰርቴፍኬት አይደለም፤ የጋብቻ ሰርቴፍኬት ትዳሩን ህጋዊ ያደርገው እንደሆነ እንጂ ራሱ ትዳር ሊሆን የሚችል ነገር አይደለም። ሀገርም እንደዚያ ነው፤ ያለ ህገ መንግስት ሀገር ሊኖር ይችላል፤ ሀገር ከሌለ ግን ህግ መንግስት የሚባል ነገር አይኖርም። ህገ መንግስት የተፈጠረው በጣም ትናንት በሚባል ጊዜ ሲሆን፤ ሀገሮች የተፈረጡትና የኖሩት ግን ለብዙ ሺህ ዓመታት ነው። ለምሳሌ፤ የእኛ ሀገር ታሪክ ብንወስድ እንኳ የሀገሪቷ ታሪክ ከሶስት
ሺህ ዓመት በላይ ሲሆን በህገ መንግስት ስም መተዳዳር የጀመርንበት ጊዜ ሲታይ ደግሞ አንድ መቶ ዓመትም አልሞላንም። ለነገሩ በሀገራችን በጠመንጃ ጉልበት እንጂ በአግባቡ በህገ መንግስት የሚያስተዳድረን መንግስት እስከዛሬ አላገኘንም ወይም አልፈጠርንም።

2.ስለኤርትራውያን
አቦይ ስብሀት ስለኤርትራውያን ሲናገሩ «ኤርትራውያን ከኢትዮጵያውያን በላይ ነው ኢትዮጵያዊነትን በጣም ይፈልጋሉ፤ በአንፃሩ ኢትዮጵያውያን የሚፈልጉት የኤርትራ መሬት ነው ህዝቡ አይደለም። አሰብ ቀይ ምናምን ይላሉ።» ብለው እርፍ! ምንም እንኳ ንግግሩ እጅግ በጣም የሚገርም ቢሆንም የአርትራውያንን ኢትዮጵያዊነት ከአቦይ ስብሀት መስማቴ ጥሩ ለውጥ ነው እላለሁ፤ ኤርትራውያን ከእኛ በላይ፣ ከኢትዮጵያውያን በላይ ኢትዮጵያዊነትን ይሰማቸዋል የሚለውን ግን ቀልድ ነው ሊሆን የሚችለው። ሲጀመር እንዲህ ብሎ ለመናገር በመጀመርያ ህዝቡ ስለዚህ ጉዳይ ያለው አቋም ተጠንቶ፤ በደንብ በተጠናቀረ መረጃ ተደግፎ ነው መቅረብ የነበረበት። ከሁሉም በላይ እጅግ አድርጎ የሚያሳዝነው ደግሞ ኢትዮጵያውያን የኤርትራን መሬት እንጂ ህዝቡ አይፈልጉትም መባሉ ነው። እኔ የማውቀው በተቃራኒው ነው፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ለኤርትራውያን ጥልቅ የሆነ ፍቅር እንዳለው ነው፤ አሁን ይሄ ሁሉ ነገር ከተፈጠረ በኋላ እንኳ እንደ ራሱ ህዝብ እንደወንድም ህዝብ እንጂ እንደ ጎሮቤት ህዝብ ወይም እንደባዕድ ህዝብ የሚያያቸው አይደለም። አቦይ ስብሀት የኤርትራ እና የኢትዮጵያ ህዝቦች የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ነገሮች እየሰከኑ ሲሄዱ ለምሳሌ በኤርትራ ያለውን ስርዓት ሲቀየር በሆኑ ቅርፅ ተባብረው የፖለቲካና የኢኮኖሚ ግንኙነታውን ማጠናከር የሚችሉበት እንድል እንዳለ፤ በፌዴሬሽንም በኮንፌደረሽንም በሌላም መልኩ የነበራቸውን አንድነት መመለስ የሚችሉበት ሁኔታ ይፈጠራል ብለው እንደሚያምኑ የተናገሩት በዚያን ቀን ከተናገሯቸው አዎንታዊ ንግግሮች አንዱ ነበር። ስለ ኤርትራው ፕሬዚደንት ሲናገሩ ኢሳይያስ የሚፈልገው አጀብና እዩኝ እዩኝ ማለት እንጂ ሌላ ነገር አይደለም ብሏል፤ እርሱ ገንዘብም አይፈልግም ብሏል። የምን ገንዘብ እንደሆነ ግልፅ ባያደርጉትም የእርዳታ ገንዘብ ማለታቸው ሊሆን እንደሚችል መገመት የሚቻል ነው። ሀበሻ አይደሉ፤ እኛ እና እርሱ ልዩነታን እዚህ ላይ ነው ማለታቸው መሆን አለበት በቅኔ!
ይልቅ የሰሞኑ አንዱ ገጠመኝ ልንገራችሁ አንድ ኤርትራዊ ከሳውዲ አረቢያ ኢትዮጵያዊ ነኝ ብሎ ከኢትዮጵያውያን ጋር ተደባልቆ እንደመጣ ሲነግሩኝ፤ እንዴት ነው ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ኢትዮጵያውያንን የሚለዩበት ብልሀት አጥተው ነው ወይስ የኤርትራውያን ኢትዮጵዊነት ተቀብለው ነው እንደዚህ ወጣት ያሉ ኤርትራውያን በነፃ ከእኛ ዜጎች ጋር ወደ ሀገራችን እያመጡ ያሉት ያስባል። ሻዕቢያ ካልላካቸው ምንም ችግር የለውም፤ ኢትዮጵያም ሀገራቸው ነው። ድሮም ቢሆን በሻዕቢያ ፕሮፖጋንዳ ተታልለው ነው እንገንጠል ብለው የሄዱት እንጂ የኢትዮጵያ ህዝብ ስለጠላቸው አልነበረም። አቦይ ስብሀት እንዳሉት እነዚህ ኤርትራውያን እየመጡ ያሉት ትክክለኛ ኢትየጵያውያን እነርሱ ናቸው ተብሎ ከሆነ ግን በማን መንግስት እየተዳደርን እንደሆነ መጠየቃችን አይወሬ ይሆናል። «እናንተ ከኤርትራውያን ያነሳችሁ ኢትዮጵያውያን ናችሁ» የሚለን መንግስት መቼውም ቢሆን ጤነኛ መንግስት ሊሆን አይችልም፤ የእኛ መንግስትም የመሆን እድል የለውም።

3. የቀበጡ ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች
በእስር ላይ ስለሚገኙ ጋዜጠኞችና ፖለቲከኞች ተጠይቀው ሲመልሱ «ይሄ ስርዓት በስንት መስዋዕትነት የመጣ ስርዓት ነው፤ በዚህ ላይ ሁኔታ በመጣ ስርዓት ላይ ማንንም እንዲቀብጥ ሊፈቀድለት አይገባም። መለስ በፓርላማ ስላንዳንድ ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች አስመልክቶ ሲናገር ጉዳት እስካላደረሱ ድረስ ወንጀለኛ መሆናቸውን እያወቅንም እንታገሳቸዋለን ሲል ሰምታችሁት ይሆናል ተሳስቷል። ማንም ሰው በህገ መንግስቱ ላይ በስርዓቱ ላይ የመቅበጥ ምልክት ሲያሳይ ጊዜ ሊሰጠው አይገባም፤ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል። ስለዚህ ማንም ቀበጥ በስርዓቱ ላይ እንዲጫወትበት አንፈቅድም» ብሏል። እንግዲህ በእርሳቸው አባባል
ከሄድን እነ አንዷለም አራጌ፣ እነ ርዕዮት ዓለሙ፤ እነ ውብሸት ታዬ፣ እነ እስክንድር ነጋ በቅብጠት ነው የታሰሩት ማለት ነው። በእስር ጉዳይ ላይ ቀብጠት አለ እንዴ! ለዚያውም በእኛ ሀገር! የኖርዌይ መንግስት እንደዚያ ቢል ብዙም ላይገርም ይችላል፤ ምክንያቱም የእስር ቤታቸው ሁኔታ እጅግ የሚያማልል ነው። ከእኛ አንፃር ስታየው! በቃልቲ ለመታሰር እንዴት ነው ቅብጠት የሚሆነው። እነርሱ የታሰሩት የነፃነት የፍትህ ጥያቄ እንስተው እንጂ ቀብጠው አይመስለኝም። እኔም ይሄን ጉዳይ አንስቼ ቅብጠት ሊሆን እኮ ነው በአቦይ ስብሀት አተያይ! ጠያቂው በመቀጠል «እነዚህ የታሰሩት ጋዜጦኞች በአንድ በእኩል ወንጀለኛ ተብለው ታስሯል በሌላ በእኩል የሀሳብን በነፃነት የመግለፅ ታጋዮች ተብለው በዓለም አቀፍ እየተሸለሙ ነው ይሄ ሁለቱ ነገር አይጋጭም ወይ?» ብሎ ሲጠይቃቸው፣ ፈገግ ብለው ያሰራው አካል እኮ አይደለም እየሸለማቸው ያለው! በማለት ተሳልቋል።

4. ስለሰማያዊ ፓርቲ
«ሰማያዊ ፓርቲ የምን ፓርቲ እንደሆነ ግራ የሚገባ ነው፤ የሃይማኖት ፓርቲ ይሁን የፖለቲካ ፓርቲ ይሁን አይታወቅም» አሉ። በመቀጠል ደግሞ «ሰማያዊ ፓርቲ ሙስሊም ወንድሞቻችን ሲል ሰምታችሁ ይሆናል። እነርሱ ናቸው የሞስሊሞች ወንድም የሚሆኑት! አቤት ሙስሊሞቹ ሲጠሏቸው ብታዩ! ወደ እኛ እየመጡ ለምን እንዚህን አታሳርፉልንም ነው እኮ የሚሉን።» በማለት ተናግሯል። እዚህ ላይም መረጃ ሰብስበው ጥናት አድርገው አይደለም የተናገሩት። የተወሰኑ ሙስሊም ጓደኞቻቸው ጋር በጉዳዩ ላይ እውርተው ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን በጣት የሚቆጠሩ ሙስሊሞች በዚህ ጉዳይ ላይ ያላቸውን ሀሳብ ማወቅና በብዙ ሚሊዮን የሚገመቱ ሙስሊሞች ለሰማያዊ ያላቸውን አመለካከት ማወቅ የተለያየ ነገር ነው።

5. ስለሀብት ክፍፍል እና ስለኢህአዴግ ርዕዮተ ዓለም
ስለሀብት ክፍፍል ሲናገሩ ደግሞ «በአለም አንደኛ ፍትሀዊት ሀገር ዶብብ ኮርያ ስትሆን፤ ኢትዮጵያ ደግሞ ሁለተኛ ናት፤ አሜሪካ ደግሞ የመጨረሻዋ ነች አሉ። እንግዲህ አሜረካን በደንብ የምታውቁ መስክሩ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ስላለው ሁኔታ እንኳ በቅርብ እናውቀዋለን፤ ምስክር መጥራት የሚያስፈልገን ነገር አይደለም። አቦይ ስብሀት ስለኢህአዴግ ርዕዮተ ዓለም ሲናገሩ፤ «ኢህአዴግ ቀኝ ዘምም ግራ ዘመምም አይደለም፤ ‘centrist’ ነው ‘pragmatic’ ነው» አሉ። አቶ ልደቱ አያሌው «ሶስተኛ አማራጭ» የሚሉትም ይሄ “centrist” የሚባለውን በሌበራል ዴሞክራሲ ውስጥ የሚመደብ ርዕዮተ ዓለም ነው። ማንም ሰው ወይም ፓርቲ በቀኝ አክራሪነት ወይም በግራ አክራነት ላለመመደብ በስም “centrist” መባለን ይፈልጋል። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን በእኛ ሀገር በትክክል “centrist” ሊባሉ የሚችሉ ፓርቲዎች ያሉ አይመስለኝም። በፓርቲው ውስጥ ወደ ቀኝ ጥግ የመሄድ ዝንባሌ እንዳለ ሆኖ በፕሮግራም ደረጃ ወደ “centrist” የሚጠጋ አቋም ያለው አንድነት ፓርቲ ብቻ ይመስለኛል። ሌላው ሁሉ አንድም በቀኝ፣ አንድም በግራ የሚመደብ ነው። የኢህአዴግ እንኳ ግራ ዘመምም ለመሆኑ ክርክር ውስጥም የሚገባ አይደለም። አቦይ ስብሀት ወደ ጫካ ሲገቡ እድሜያቸው ሰላሳ ዘጠኝ እንደነበረ ራሳቸው በዚያው መድረክ ላይ የተናገሩ ሲሆን አስራ ሰባት ዓመት በትግል 23 ዓመት ደግሞ በስልጣን የቆዩ ከመሆናቸው አንፃር አሁን የሰባ ዘጠኝ ዓመት አዛውንት ናቸው ማለት ነው። ነገር ግን አሁንም ጠንካራ እንደሆኑ ታዝቤያለሁ፤ የዓይን መነፅር እንኳ ሳያድርጉ ነው ሲንቀሳቀሱ የነበረው። ነገር ግን አነጋገራቸው ሁሉም አይቶ እንዳሳለፈ ሰው ሆኖ አላገኘሁትም፤ ይልቅ ገና የፖለቲካ ስሜቱ እንዳልነበረደለት ጎረምሳ ነው በትዕቢትና በማን አህሎኝነት ሲናገሩ የነበሩት። በተለይ ስለተቃዋሚዎች ሲናገሩ ያላቸውን ጥላቻ በግልፅ ያስታውቅ ነበር። ጥላቻ በዚህ ዕድሜ በጣምም ጥሩ አይደለም።

~~ምንጭ ፥ ethiomedia.com~~

Advertisements